ቀጥታ፡

የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስስር ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው- የሰላም ሚኒስቴር

ደሴ ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፡-የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስስር  የጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች  ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር   ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ወሎ የኒቨርሲቲ ከደሴ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር "የወሎ ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስሰር" ምስረታ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር  የብሔራዊ መግባባት ዴስክ ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ዘቢባ የሱፍ  እንደገለጹት ፤ ሚኒስቴሩ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር አበክሮ እየሰራ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ሥራዎች በተጓዳኝ በሚያካሂዷቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች የኢትዮጵያውያን የአብሮነት፣ የፍቅርና የመቻቻል እሴቶች  እንዲጎለብቱ እያገዙ መሆኑን አንስተዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም እየተስፋፋ የመጣው "የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስስር" አበረታች ውጤት እያመጣ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተሞክሮውን በማስፋት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተተግብሮ  ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ዛሬ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመሰረተው  የቃል ኪዳን ትስስር የወሎን የአብሮነት፣ የፍቅርና የመቻቻል ባሕል በማስቀጠል ተማሪዎች በቆይታቸው ከቤተሰባቸው ጋር እንዳሉ እንዲሰማቸው ብሎም የወሎን ባሕልና ወግ ለማስተዋወቅም ያግዛል ብለዋል።


 

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ብርሃን አስማሜ(ዶ/ር)  በበኩላቸው፤ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳሉ ተሰምቷቸው ተረጋግተው መማር እንዲችሉ የተመሰረተው የ"ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስስር " ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ትስስሩም  "የወሎ ቃል ኪዳን ቤተሰብ " የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ በትስስር የሚያቅፋቸውን ተማሪዎች እንደ ልጁ በመንከባከብ፣ በማገዝና በመደገፍ ተረጋግተው እንዲማሩ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ካሳው፤ የቃል ኪዳን ትስስሩ ተማሪዎችን ከሕብረተሰቡ ጋር በማስተሳር ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ ይደረጋል  ሲሉ አብራርተዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እንደ ልጆቻችን በመንከባከብና በማስተማር ለቁም ነገር እንዲበቁ ለማድረግ  የድርሻችንን እንወጣለን ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ   አቶ ልዑል ይማም ናቸው።

ወይዘሮ መሰረት ታደሰ በበኩላቸው ፤ ቀደም ሲልም ተማሪዎችን በመቀበል ቤተሰባዊ ትስስር ይፈጥሩ እንደነበረ አስታውሰው፤  ይህንን ተግባር እንደሚቀጥሉበትም  ገልጸዋል።

በመድረኩ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም