ቀጥታ፡

በሰሜን ወሎ ዞን የክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ወቅት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ወልዲያ ፤ ጥቅምት 22/2018 (ኢዜአ)፡- በሰሜን ወሎ ዞን  የክረምቱ  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ በጋውም በመሸጋገር  ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

ባለፈው የክረምት ወቅት ከ326 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረገ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑን መምሪያው አመላክቷል።  

በመምሪያው  የወጣቶች ማካተትና ንቅናቄ ተሳትፎ ቡድን ባለሙያ አቶ ዮርዳኖስ ደምሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትንና መደጋገፍን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው። 

ይህንን ተግባር ለማጠናከር በተያዘው የበጋ ወቅት ከ164 ሚሊዮን  ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከ303 ሺህ የሚበልጥ  ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።  

ከመስከረም 25/2018 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 20 ቀናት ውስጥ ብቻ የ11 አቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች ጥገናና በአዲስ የመገንባትና የ15 ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦይ  የማጽዳት ስራ ማከናወን መቻሉን አንስተዋል።

በግብርናው ዘርፍም የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል። 

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ፣ የትምህርት ተደራሽነትን የማስፋትና የደም ልገሳ መከናወኑን ጠቅሰዋል። 

አርሶ አደር አስፋዬ ተሰማ በዞኑ የጉባላፍቶ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሰሞኑን ወደ እርሻ  መሬታቸው ውሃ የሚያስገባውን የመስኖ ቦይ በመጥረግ  ለልማት  ዝግጁ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል። 

ይህም መሬቴን በወቅቱ በሰብል በመሸፈን ተጨማሪ ምርት በማምረት ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት እንደሚያስችላቸው  በመግለጽ፤ ለወጣቶቹ  ምስጋና አቅርበዋል። 

የሐብሩ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ አራጋው በበኩላቸው፤  በጎ ፈቃደኞች  በአገልግሎት ብዛት አርጅቶ የተጎዳውን የሣር ክዳን ቤታቸውን በአዲስ ቆርቆሮ በመተካት ጭምር የተሻለ  አድርገው እንደሰሩላቸው ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው የክረምት ወቅት በተከናወነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 326 ሺህ 110 ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም