በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ዕድል መፍጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ፕሮጀክቶች ዕውን መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገርን ከጸጋዎቿ በማሰናሰል በብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት ዕመርታዊ ውጤት ማስመዝገብ ያስቻሉ የአሰራር ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን አስረድተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ እንደሚያስችላት ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ከአዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የዕድገት ምጣኔ ከሁለት አሃዝ በላይ ዕድገት እያሳየ መጥቷል ብለዋል።
ይህም ለሀገር ውስጥ የምርት ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር አስችሏል ነው ያሉት።
አምራች ኢንዱስትሪው በተኪ ምርት፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብና በሌሎች ዘርፎችም የተሻለ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መዋቅራዊ ሽግግሩ በፈጣን ሁኔታ ለውጥ በማሳየት ዘርፉ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ሃላፊዎች መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የቡም ማኑፋክቸሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ጸጋ ደበበ እንዳሉት፤ መንግስት ለአምራች ዘርፉ ትኩረት መስጠቱ የሚያበረታታ ነው፡፡
ኩባንያው ከተመሰረተ ሁለት ዓመት እንዳለፈው በመግለጽ፤ በዋናነት ለቤት ውስጥ ግልጋሎት የሚውሉ የማቀዝቀዣ ምርቶች እያመረተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም በሀገር ውስጥ የሚያመርቱት የኢንዱስትሪ ውጤት ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በመተካት በኩል የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኤች ኬ ቢዝነስ ግሩፕ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኮርፖሬት ዳይሬክተር ብሩ ኢርቱ በበኩላቸው፤ ተኪ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሪ በማዳን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በዋናነት ለኮንስትራክሽን ግንባታ የሚውሉና ከፕላስቲክ የሚመረቱ ፎርም ዎርኮችን በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት ከዚህ ቀደም ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያስቻላቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡