ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ አርሰናል ከበርንሌይ ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2018 (ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።

የሊጉ መሪ አርሰናል ወደ ተርፍ ሙር ስታዲየም በማምራት ከአዲስ አዳጊው በርንሌይ ጋር ይጫወታል።

አርሰናል በ22 አንደኛ፣ በርንሌይ በ10 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ19ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 18 ጨዋታዎች አርሰናል 13 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በርንሌይ አንድ ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።’

በድንቅ ብቃት ላይ የሚገኘው አርሰናል ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል።

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው በርንሌይ በጨዋታው ጥሩ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የ40 ዓመቱ ክሪስ ካቫናግ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች ኖቲንግሃም ፎረስት ከማንችስተር ዩናይትድ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

መርሃ ግብሩ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ በድል ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርገው ነው።

በአንጻሩ በሊጉ አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው እና በውጤት ቀውስ የሚገኘው ኖቲንግሃም ፎረስት ሶስት ነጥብ እጅጉን ያስፈልገዋል።

ክሪስታል ፓላስ ከብሬንትፎርድ፣ ብራይተን ከሊድስ ዩናይትድ እና ፉልሃም ከዎልቭስ በተመሳሳይ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ከምሽቱ 5 ሰዓት በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም አስቶንቪላን ያስተናግዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም