ቀጥታ፡

የሰላም ግንባታ እና ልማትን የጋራ ስራችን አድርገን እንቀጥላለን

ደብረማርቆስ፤ መስከረም 24/2018 (ኢዜአ)፡-የሰላም ግንባታ እና ልማትን  ለማንም የማንተዋቸው የጋራ ስራችን አድርገን እንቀጥላለን ሲሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የመንግስትን የሰላም ጥረት በመግፋት ለግጭትና ጦርነት የሚሰሩ አካላት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌላቸውና ሊወገዙ የሚገባቸው መሆኑንም ነዋሪዎቹ አንስተዋል። 

በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው ያለውን የሰላም ጥረትና አጠቃላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ደረሰ ታገለ፣ ወይዘሮ እናቴነሽ አያልነህ እና አቶ አያሌው ስንሻው፤ የሰላም እጦት የሚያስከትለውን ጉዳትና ኪሳራ ደጋግመን ያየነው በመሆኑ ለሰላም መትጋትና በጋራ መስራት የግድ መሆኑን አንስተዋል።

በአካባቢው ለዘረፋ እና ለጥፋት ተልዕኮ የሚንቀሳቀሱ አካላት የነበሩ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ ብርቱ ጥረትና በህብረተሰቡ ትብብር በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ውጤታማነት እያንዳንዳችን ከመንግስት ጎን በመሆን መስራት አለብን ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የህዝብን ሰላም በመንሳት ልማትን ለማስተጓጎል በውስጥና በውጭ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ እንታገላለን ብለዋል።

የሰላም ግንባታ እና የልማት ጉዳይ ለማንም የማንተዋቸው የጋራ ሥራዎቻችን አድርገን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም