በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችንና ማሕበረሰቡን የሚያስተሳስር የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችንና ማሕበረሰቡን የሚያስተሳስር የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተመሰረተ

ደብረብርሃን፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና ማሕበረሰቡን የሚያስተሳስር “የሸዋ ብርሃን የቃል ኪዳን ቤተሰብ“ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተመሰረተ።
የቃል ኪዳን ቤተሰብ መመስረቱ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ በማተኮር ለውጤት እንዲበቁ የሚያግዝ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ተቋሙ ከመማር ማስተማር፣ ከጥናትና ምርምር ባሻገር የማህበረሰብ አገልግሎትን እያጠናከረ ይገኛል።
ይህም በማህበረሰቡ ውስጥ ፀንቶ የቆየው የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህል በሳይንሳዊ መንገድ ለማስደገፍ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ከከተማው ህዝብ ጋር ለማስተሳሰር ዛሬ የተካሄደው “የሸዋ ብርሃን ቃል ኪዳን ቤተሰብ“ ምስረታ መርሃ ግብርን በአብነት ጠቅሰዋል።
ዓላማውም ፈቃደኛ ለሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ተማሪዎችን በመስጠት ልክ እንደልጆቻቸው በመንከባከብ፣ በመደገፍና ፍቅር በመስጠት ለስኬት እንዲበቁ ማድረግ ነው ብለዋል።
ዘንድሮ በሚገቡ አዲስ ተማሪዎች የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትስስሩ እንደሚጀምርም ጨምረው አስታውቀዋል።
ለስኬቱም የከተማ አስተዳደሩ፤ ተማሪዎችን ለማቀፍ ፈቃደኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከዛሬ ጀምሮ እንደሚለይም ተመልክቷል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው፤ የቃል ኪዳን ቤተሰብ መርሃ ግብር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎች የቃል ኪዳን ቤተሰብ ማግኘታቸው የአካባቢውን ወግና ባህል እንዲያውቁ፣ የሚገጥማቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር በማቃለል ተምረው ለስኬት እንዲበቁ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ተማሪዎችም በሚያገኙት አዲስ ቤተሰብ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላል ነው ያሉት።
የቃል ኪዳን ቤተሰብ መርሃ ግብር ቀድሞ በተገበረው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሚ መሆኑን በመግለፅ አስተያየቱን የሰጠው ኮከብ ደስታ፤ በዩኒቨርሲቲው አማካኝነት ያገኘው ቤተሰብ እንደወላጅ ተንከባክበው፣ ስታመም አስታመው ለቁም ነገር አብቅተውኛል ብሏል።
ወደ ስራ ከተሰማራሁ በኋላም ትስስሩን በማጠናከር ቤተሰብ ከቤተሰብ በደስታና በሀዘን ጊዜ ለመጠያየቅ እንደበቁ ጠቁሞ፤ መርሃ ግብሩ አብሮነት፣ ሰላምና ፍቅርን ለመገንባት ጠቃሚ መሆኑን አስረድቷል።