ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል

ድሬደዋ፣ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ  የሚደረገው የድጋፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የኛ ገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር ዛሬ ለ30 የአስተዳደሩ አቅመ ደካማ ህፃናት ቦርሳ፣ ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ እርሳስና ሌሎች የትምህርት መማሪያ ቁሶችን አበርክቷል።

ማህበሩ ህፃናቱን እስከ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ደረጃ በቋሚነት ለመደገፍ የሚያስችለውን ስምምነት ከድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር ተፈራርሟል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮው የክረምት ወራት ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ በአስተዳደሩ እየተደረገ የሚገኘው ድጋፍ አበረታች ነው።

ድጋፉን በቋሚነት ማስቀጠል ህፃናቱ በዕውቀትና ክህሎት ተኮትኩተው የነገ አገር ገንቢና ተረካቢ ዜጎች እንዲሆኑ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

ይሄንን መሠረታዊ ጉዳይ ዕውን ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።

የህብረት ስራ ማህበሩ ዛሬ ያደረገው ስምምነትና ድጋፍ ለሌሎች መሰል ተቋማት ምሳሌ እንደሚሆንም እንዲሁ።

ማህበሩም ሆነ የትምህርት ባለድርሻዎችና ባለሃብቶች በቀጣይ በሚካሄደው የትምህርት ቤት ምገባ ላይ የድርሻውን ሚና እንዲያጠናክር አቶ ሱልጣን ጠይቀዋል።

የእርስ በእርስ የመደጋገፍና የመረዳዳትን ባህላዊ እሴትን ማጠናከር የትኛውንም ማህበራዊ ችግር በራስ አቅም ለመፍታት ያስችላል ያሉት ደግሞ የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳንኤል ታደሰ ናቸው።

የትምህርት መማሪያ ድጋፍ ከተሰጣቸው መካከል ህፃን ሐያት አብዱረህማን በተደረገው ድጋፍ የተሰማትን ደስታ ገልፃ ለትምህርቷ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግራለች ።

አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው በበኩላቸው ልጄን በቋሚነት የሚደግፍ አካል በማግኘቴ እኔም ለልጄ ትምህርትና ስነምግባር ልዩ ስፍራ በመስጠት ድጋፍና ክትትሌን አጠናክራለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም