በ2017 የትምህርት ዘመን በመሰረተ ልማት ማስፋፊያ እና በትምህርት ጥራት ስኬቶች ተመዝግበዋል-የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በ2017 የትምህርት ዘመን በመሰረተ ልማት ማስፋፊያ እና በትምህርት ጥራት ስኬቶች ተመዝግበዋል-የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ):- በመዲናዋ በተጠናቀቀው የ2017 የትምህርት ዘመን በትምህርት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ እና በትምህርት ጥራት ስኬቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምሀርት ዘመን አፈፃፀም እና 2018 ዓ.ም እቅድ ላይ ለዘርፉ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመዲናዋ በትምህርት ዘርፉ በርካታ የመማር ማስተማሩን ስኬታማ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት በተከታታይ መተግበሩ እና የተሟላ ትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ተደራሽ መሆኑ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የጎላ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል።
ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን በመተግበርም ዘንድሮ በስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ የውጤት መሻሻል መታየቱን አብራርተዋል።
የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ የመማሪያ አካባቢዎችን የማዘመን ሥራ መከናወኑንም ነው የቢሮ ኃላፊው ያነሱት።
ለትምህርት መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት የነባር ትምህርት ቤቶችን ማሻሻያ እና አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መከናወኑን አስረድተዋል።
በዚህም በዓመቱ በመዲናዋ 37 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄም የመዲናዋን ትምህርት ቤቶች ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ቢሮው አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳደግ የመምህራን ልማት ላይ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመንም ትውልድን በእውቀት እና በስነ ምግባር የማነጽ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት መምህርት አይናዲስ ዘለቀ በበኩላቸው የተማሪዎች ምገባ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ እና እንዳያረፍዱ በማስቻል በውጤታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የተሻለ ትውልድ ለመቅረጽ እንደሚሰሩ ገልጸው፥ የመምህራን አቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አብደላ ቡልቡላ በበኩላቸው ለትውልዱ ምቹ የመማሪያ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ መሆኑ የሚያኮራ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶችን ከማሻሻል አንጻር እንደሙያተኛ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።