በጋምቤላ ክልል ከ15 ሺህ በላይ የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ከ15 ሺህ በላይ የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ነው
ጋምቤላ፤ ሰኔ 11/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ከ15 ሺህ በላይ የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና መውሰድ መጀመራቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡኩን ኡኬሎ ለኢዜአ እንደገለፁት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የስድስተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ዛሬ መሰጠት መጀመሩን ገልፀዋል።
በ262 የፈተና ጣቢያዎች ከ15 ሺህ 100 የሚበልጡ ተማሪዎች ክልል አቀፋን ፈተና እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ክልል አቀፉን የ6ኛ ክፍል ፈተና ከሚወስዱት ተማሪዎች መካከል 6 ሺህ 578 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውም አመላክተዋል።
ክልል አቀፉ የስድስተኛ ክፍል ፈተና በሰባት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እየተሰጠ መሆኑንም ገልፀው የፈተናውን ሂደት የሚያስፈጽሙ 719 ፈታኞችና ሱፐርቫይዘሮች መሠማራታቸውን ተናግረዋል።
የስድስተኛ ክፍል ፈተና መስጠት መጀመሩ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ገልፀዋል።
ክልል አቀፍ ፈተናው ሰኔ 11 እና 12 ተሰጥቶ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅም አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ብለዋል።