ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 378 ቦታዎች ተለይተዋል- ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ በከፍተኛ ደረጃ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 378 ቦታዎች መለየታቸውን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚደርሱ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች መካከል ጎርፍ፣ እሳት፣የመሬት መንሸራተትና የትራፊክ አደጋ ይገኙበታል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ባለፉት አመታት በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

የዘንድሮ ክረምትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ አቅዷ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይገልጻል።

የኮሚሽኑ የአደጋ ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ደሳለኝ ቱፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ክረምትን ተከትሎ በመዲናዋ ሊከሰት የሚችል ጎርፍን መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን አንስተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ህብረተሰቡ ከወንዝ ዳርቻ በመራቅ፣የተደፈኑ ትቦዎችን በመክፈት፣ ቆሻሻን በአግባቡ እንዲያስወግዱ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች መሰራታቸውንም ገልፀዋል።

በመዲናዋ በከፍተኛ ደረጃ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ እንደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ የአቃቂ ቃሊቲ፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 378 ቦታዎች መለየታቸውን ገልጸው፤ 170 የሚሆኑት ላይ የማስተካከል ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በእነዚህ ቦታዎች የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡም በክረምቱ ለጎርፍ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒካሽን ዳይሬክተር እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው፤ በክረምት ወቅት ከተራራማ አካባቢዎች የሚመጣ ጎርፍ በመንገዶች ብሎም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ ሊያደርስ የሚችልበት ሆኔታ ይኖራል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ብልሽት ያጋጠማቸው መንገዶችና ድልድዮች የመጠገን እና በቆሻሻ የተደፈኑትን የውሃ ማፋሰሻ ትቦዎችን የማፅዳት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ጠቅሰዋል፡፡

አቶ እያሱ አክለውም፥ የተሰራው የቅድመ-መከላከል ስራ ጎርፍ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን የመንገድ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቆሻሻን በፍሳሽ ማስወገጃዎች ላይ ከመጣል በመታቀብ በቆሻሻና በደለል የተደፈኑትንም ትቦዎች በማፅዳት ራሱን ከጎርፍ አደጋ እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም