በክልሉ ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የዓይን ህክምና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የዓይን ህክምና እየተሰጠ ነው
መቐለ፤ ጥር 14/2014 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የዓይን ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ተገለፀ።
የዓይን ህክምና አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር በሚገኙ የጤናና የትምህርት ቢሮዎች በቅንጅት "ላይፍ ፎር ዘ ወርልድ" ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑም ተገልጿል።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ የ"ላይፍ ኦፍ ዘ ወርልድ" አስተባባሪ አቶ በሪሁ ገብረማርያም ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በህፃናት ተማሪዎች ላይ የሚከሰተውን የዓይን በሽታ ለመከላከል ከምርመራ እስከ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
አገልግሎቱ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በማዕከላዊ፤ በደቡብ ምስራቅ ዞኖችና በመቐሌ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ 30 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ገልፀዋል።
በትምህርት ቤቶቹ ለሚያስተምሩ 200 መምህራንም በዓይን ጤንነት ላይ ሊተገብሯው በሚገቡ የዓይን በሽታ መከላከያ ዘዴዎች ዙሪያ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል።
ለተማሪዎቹ እየተሰጠ ያለው የዓይን ህክምና አገልግሎት ለሁለት ዓመታት እንደሚቀጥል ገልፀው፤ የዕይታ መዳከም ለታየባቸው 200 ተማሪዎች ደግሞ የዓይን መነፅር በነፃ መሰጠቱንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ "ላይፍ ፎር ዘ ወርልድ" አስተባባሪ አቶ እዩኤል ለማ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የዓይን ዕይታ ችግር ያለባቸው ዕድሜያቸው እስከ15 ዓመት የሆኑ ተማሪዎችን ችግር ለማቃለል እየሰራን ነው ብለዋል።
አገልግሎቱን ለመስጠት የተፈለገውም ከመማር ማስተማር ጋር በተያያዘ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች የዓይን ዕይታ ለማስተካከል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ትግራይን ጨምሮ በሌሎች አምስት ክልሎች ለ120 ሺህ ተማሪዎች የዓይን የምርመራ አገልግሎት መሰጠቱን አውስተዋል።
ምርመራ ከተደረገላቸው አጠቃላይ ተማሪዎች ከ800 በላይ የሚሆኑት ዕይታቸው ተዳክሞ በመገኘቱ የዓይን መነፅር እንዲጠቀሙ መደረጉን ተናግረዋል።
በአክሱም ከተማ በመጋቢት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዓይን መነፅር ከተሰጣቸው ተማሪዎች መካከል የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሙሴ ሓጎስ የዕይታ አቅሙ ተዳክሞ ትምህርቱን ለመከታተል ይቸገር እንደነበር ተናግሯል።
የዓይን መነፅር ከተሰጠው በኋላ ትምህርቱን በሚገባ ለመከታተል እንዳስቻለው ገልጿል።
ተማሪ ዮርዳኖስ መብራህቱና ተማሪ አሰፋ ወልደ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ መንገድ ችግሮቻቸው መቃለሉን ገልፀዋል።