ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለመገንባት የብሔረሰቦችን እሴትና የሕግ የበላይነትን ማክበር እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለመገንባት የብሔረሰቦችን እሴትና የሕግ የበላይነትን ማክበር እንደሚገባ ተገለጸ

ቴፒ ፤ህዳር 22/2017 (ኢዜአ):- ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለመገንባት የብሔረሰቦችን እሴትና የሕግ የበላይነትን ማክበር እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኮ ገለጹ።
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቴፒ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኮ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት የብሔረሰቦችን ባህልና ወግ ለመጠበቅ ብሎም ለማልማት ሕገ መንግስቱ አስቻይ ሁኔታዎችን የፈጠረ ነው።
19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕገ መንግስትና የፌዴራሊዝም ሥርዓት ላይ ግንዛቤ በመፍጠርና የአብሮነት እሴቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ በክልሉ መከበሩን ገልጸዋል።
በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለመገንባት የብሔረሰቦችን እሴትና የሕግ የበላይነትን ማክበር እንደምገባ አስገንዝበዋል።
ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲጎለብት በማድረግ የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር የበዓሉ ዓላማ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለክልሉ ብሎም ለሀገር ሰላምና አንድነት መጎልበት ብዝኃነት ውስጥ የሚፈጠሩ የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ በጋራ መጓዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የሕግ የበላይነትና ብዝኃነትን ማክበር እንደሚገባ የጠቀሱት አፈ ጉባኤው የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ለሁለንተናዊ ብልጽግና ያለው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ከኮንታ ዞን የመጡት አቶ በላይ ዶጮ የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሕገ መንግስቱ የተጠቀሱ መብቶችና የብሔረሰብ ማንነቶች መከበርን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
"የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንዱ የአንዱን ማንነትና እሴት በመጋራት የሚተዋወቁበት ምቹ አጋጣሚና ሕዝቦች አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ነው" ብለዋል።
"የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእኩልነት መገለጫ ነው" ያሉት ደግሞ የቴፒ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ንጋቷ ታደሰ ናቸው።
ቀኑን ከማክበር ባሻገር ፍቅርና አንድነትን በመያዝ ሰላምን ማጽናት ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
"ሀገራዊ መግባባት፤ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ቴፒ ከተማ በተከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች ተወካዮችና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።