የብልጽግና ፓርቲ መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና፤ መንገዱ መደመር፤ ገዥ ትርክቱም ህብረ ብሄራዊ አንድነት ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ፓርቲ መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና፤ መንገዱ መደመር፤ ገዥ ትርክቱም ህብረ ብሄራዊ አንድነት ነው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- የብልጽግና ፓርቲ መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና፤ መንገዱ መደመር እና ገዥ ትርክቱም ህብረ ብሄራዊ አንድነት መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሀ ግብር የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የፓርቲው አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም በተገኙበት ተከብሯል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፤ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር የብልጽግና ፓርቲ መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና፣ መንገዱ መደመር፣ ገዥ ትርክቱም ህብረ ብሔራዊነት መሆኑን አንስተዋል።
በሀገር በቀል እሳቤዎች ሀገራዊ አቅሞችን መጠቀም እንዲሁም አጋርነት፣ ወንድማማችና እህትማማችነትን ማጠናከር የፓርቲው እሳቤዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚሁ እሳቤ ባለፉት አምስት ዓመታት በአመራሩ ቁርጠኝነት በህዝቡ የላቀ እገዛና ተሳትፎ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ብልጽግና ባለፉት ዓመታት ብሔራዊ ወንድማማችነት እንዲሁም እውነት፣ እውቀትና ጥበብን መለያው አድርጎ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።