ቀጥታ፡

የተሻሻለው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው-ሚኒስቴሩ

ሀላባ፤ ህዳር 14/2017 (ኢዜአ)፦የተሻሻለው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ አርሶ አደሩ በተቀናጀ መንገድ መሬትን በማልማት ተጠቃሚነቱን የበለጠ እንዲያረጋግጥ የሚያስችል መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተሻሻለው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ በተመለከተ ለህግ ተርጓሚዎችና ሌሎች ባለድርሻ አከላት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይና የመሬት ህግ ባለሙያ አቶ አበባው አበበ እንዳሉት የተሻሻለው አዋጅ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ ነው።

ከዚህ ቀደም በስራ ላይ የነበረው አዋጅ ውስንነቶች የነበሩት ሲሆን የተሻሻለው አዋጅ ግን የአምራቹን ምርታማነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ ብለዋል።

ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ቋት መበልጸጉን ጠቅሰው አርሶ አደሩ ሳይቸገር መሬቱን ለተለያዩ ግልጋሎቶች በማዋል እንዲጠቀም የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ ካሉት ከ50 ሚሊዮን በላይ ማሳ በእስከ አሁኑ ሂደት ከ32 ሚሊዮን በላይ የተለካ ሲሆን ከ7 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የመሬት ባለቤትነት የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውንም አስረድተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ክልሉ ያሉትን አቅሞች በማቀናጀት ድህነትን ለማሸነፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።


 

አዋጁ አርሶ አደሮችንና ኢንቬስተሮችን እንዲሁም አቅመ ደካሞችንና ሴቶችን ጨምሮ አካታች በሆነ መልኩ ሁሉንም ዜጎች በመሬት ላይ ያላቸውን ፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚነት የሚያሰፋ መሆኑንም አንስተዋል።

አርሶ አደሩ ጊዜውንና ጉልበቱን በልማት ላይ እንዲያሳልፍ የህግ ተርጓሚው አዋጁን በውል አውቆ በመተግበርና በማገዝ ለተጀመረው የልማትና የብልጽግና ግብ ስኬት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጄንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልሀፍዝ ሁሴን በክልሉ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ማሳ ተለክቶ ማረጋገጫ እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል።


 

ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ መሬታቸውን አስይዘው ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ከ324 ሚሊዮን ብር በላይ መመቻቸቱን ጠቁመዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ በበኩላቸው በክልሉ የዳኝነት አገልግሎት ቀልጣፋና ፍትሃዊ እንዲሁም ተገማች እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረው በዚህም አርሶ አደሩ በልማት ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ የሚጠበቅብንን እየተወጣን ነው ብለዋል።


 

በመድረኩም ከክልሉ የተውጣጡ ዳኞችና የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም