ቀጥታ፡

የልጃገረዶች ራዕይ እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመደገፍ ሊረባረቡ እንደሚገባ ተመለከተ

ባህርዳር፤ ጥቅምት 16/2017(ኢዜአ)፡- ልጃገረዶችን  በማስተማርና በመደገፍ ራዕያቸው እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመለከተ።

"ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የታዳጊ ልጃገረዶች  ቀን ዛሬ በባህር ዳር  ከተማ ተከብሯል።

በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሴት ልጆች ሊደርስባቸው ከሚችል ፆታዊ ጥቃት መጠበቅ፣ መንከባከብና ማስተማር የሁሉም ህብረተሰብ ድርሻ ሊሆን ይገባል።

የልጃገረዶች ቀን ስናከብርም እናቶቻችንን፣ እህቶቻችንና፣ ልጆቻችንን በማሰብ መሆን አለበት ያሉት ኃላፊዋ፤ ሴት ልጆች በትምህርት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱና ለኢትዮጵያ ብልፅግና ጉዞ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ  ማገዝ  ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህም የልጅነት ጋብቻና ፆታ ተኮር ጥቃትን በመቀነስ ሴቶች በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ  በማድረግ ለአገር ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ በመስራት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

ቢሮውም ታዳጊ ሴቶች በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ባለሃብቶችን በማስተባበር የመደገፍ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ የበለፀገች አገር ለመገንባት ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራትና ማስተማር የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተስራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤በተለይ የልጃገረዶች ራዕይ እንዲሳካ ወላጆችና ሌላውም ህብረተሰብ በመደገፍ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሴቶችና ህፃናት ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት  በክልሉ ፍትህ ቢሮ የሰብአዊ መብት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አለነ ናቸው። 

ፆታዊ ጥቃት ተፈፅሞ ሲገኝ በአጥፊዎች ላይ ተገቢው ፍትህ እንዲሰጥ በትብብር እየተስራ ነው ብለዋል።

በባህርዳር የሰርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሳሮን አዕምሮ በሰጠችው አስተያየት፤ የልጃገረዶች ቀን በክልል ደረጃ መከበር መጀመሩ ታዳጊ ሴቶች እንዲነቃቁ ያግዛል ስትል ገልጻለች።

"በቀጣይ በርትቼ ተምሬ ትልቅ ደረጃ በመድረስ ለችግር የተጋለጡ ሴት ህፃናትን ለመደገፍ ከወዲሁ ራዕይ ሰንቄ ትምህርቴን እየተማርኩ እገኛለሁ" ብላለች።

በፓናል ውይይት በተከበረው የልጃገረዶች  ቀን ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ተማሪዎችና ልጃገረዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም