የአሪ ዞን አስተዳደር በገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአሪ ዞን አስተዳደር በገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ
ጂንካ ፤ሀምሌ 17/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኣሪ ዞን አስተዳደር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ ።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ አመራሮች በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን አደጋው የተከሰተበት ሥፍራ ላይ በመገኘት አፅናንተዋል።
ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ350 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 20 ፍራሾች፣ 200 ሊትር ዘይት፣ 500 ኪሎ ግራም ዱቄት እና በርካታ መድኃኒቶችን ድጋፍ አድርገዋል።
የዞኑ አስተዳደር እና የኣሪ ህዝብ ለተጎጂዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በአካባቢው የደረሰው ጉዳት አስከፊ መሆኑን ተናግረው የአሪ ዞን አስተዳደር አመራሮች ተጎጂዎችን በማፅናናት ላደረጉት ሰብዓዊ ድጋፍ እና ላሳዩት ወንድማዊ ፍቅር ከልብ አመስግነዋል።
በቦታው ሌላ ጉዳት እንዳይከሰት ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች የማስፈር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ለተጎጂዎች በክልሉ መንግስት፣ በተቋማት፣ቀይ መስቀል እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፈጥኖ ደራሽ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንም አንስተዋል ።
በወረዳው በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በተደራጀ መንገድ የመደገፍ ተግባር በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉም ተመላክቷል።