ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ ጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በዚህም አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በርካታ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የመዲናዋን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።  

መሬትና ሌሎችንም የሕዝብ ኃብት ከምዝበራ በማዳን እንዲሁም ሌብነትን በመታገልም አበረታች ውጤት ተገኝቷልም ነው ያሉት። 

የግብር አሰባሰብና የክፍያ ሥርዓትን በማዘመንና በተለያዩ ሴክተሮች የዲጅታል አሰራርን በማስፋት ረገድም አበረታች አፈጻጸሞች መመዝገባቸውንም እንዲሁ።  

 በትምህርት፣ በጤና፣ በማኅበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት የተሻሉ አፈጻጸም ያላቸው ሥራዎችንም ከንቲባዋ በዝርዝር አቅርበዋል። 


 

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ማኅበረሰቡ ለሚያነሳው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ናቸው ብለዋል።

በተለይም የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየሩ ባሻገር የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ያሻሻለና ዘመናዊነትን ያላመደ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የተሻሻሉ የአሰራር ሥርዓቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም በአንዳንድ ተቋማት ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ማኅበረሰቡን ለምሬትና ለእንግልት እየዳረጉ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ፣ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሰራሮች አሁንም ውስንነቶች ያሉባቸው መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ትኩረት እንዲደረግባቸው አሳሰበዋል።

ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራው ወጥነት የጎደለው መሆኑን በማንሳት ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በቤት ልማት ዘርፍና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም የምክር ቤት አባላቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምላሻቸው፤ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ ብለዋል።

የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሰራሮችን በማስፋት የተቀላጠፈ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና የዋጋ ንረትን ለማቃለል የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።   

በተጓዳኝም፤ ከተማ አስተዳደሩ በሚያከናውነው የልማት ሥራዎች ፍትኃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ቅድሚያ መሰጠቱን ገልጸው፤ ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ የልማት ተነሺ ለሆኑ ዜጎች በቂ የካሳ ክፍያን ጨምሮ ምትክ ቤት በመስጠት ረገድ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ የሥራ ባህልን የቀየረ ከመሆኑ ባሻገር የከተማዋን የዘመናት ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እያቃለለ የመጣ በመሆኑ ተሞክሮውን በሌሎች ፕሮጀክቶች ለመድገም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በሚከናወኑ ተግባራት ነባር የጤና ተቋማትን የማጠናከርና ተጨማሪ ሆስፒታሎችን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይም በትምህርት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በከተማ ግብርና፣ በቤት ልማትና በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራ ከንቲባዋ አረጋግጠዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም