የባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው
ባህር ዳር፤ ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦ የባህዳር ዳር ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማውና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ ከተሞች ለነዋሪዎች፣ ለጎብኚዎችና እና ለሌሎች እንግዶች ምቹ የሚሆኑበት እድል የሚፈጥር ነው።
በአባይ ወንዝና የጣና ሃይቅ ዳር ላይ የተመሰረተችው ባህር ዳር ከተማ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች መሆኗ የኮሪደር ልማቱ የበለጠ ውብና ጽዱ እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል።
ለስኬታማነቱም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የባህር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ውጤታማነት በሌሎች ከተሞች ለመተግበር የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ 22 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን እንደሆነ ተገልጿል።
ዛሬ በባህር ዳር የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከባህር ዳር በተጨማሪ በሌሎች የክልሉ ከተሞችም ጭምር እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።