የ6ተኛ እና 8ተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የ6ተኛ እና 8ተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ከተፈቀዱ የፈተና ቁሳቁሶች ውጭ ዲጂታል ሰዓትን ጨምሮ ማንኛውንም ኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን እና ቀሳቁሶችን ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑንም ቢሮው አብራርቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ጫላ የ2016 ዓ.ም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና በአግባቡ ለመስጠት በተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በሁሉም የመንግስት እና የግል ትምህርት ቤቶች ሞዴል ፈተና መሰጠቱን እንዲሁም ፈተናው ታትሞ ዝግጁ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የ2016 ዓ.ም 8ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና ከሰኔ 4 እስከ ሰኔ 5 ቀን 2016 እንዲሁም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
በተለይም ተማሪዎችን ካለፈው ተሞክሮ በመነሳት በስነልቦና ከማዘጋጀት ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ ለፈተናው የሚረዱ ቅድመ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሰኔ ወር በሚሰጠው ከተማ አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ፈተና 86 ሺ 671 ተማሪዎች እንዲሁም በስድስተኛ ክፍል ፈተና 86 ሺ 217 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደገና መሰጠት መጀመሩን በማስታወስ ባለፈው ዓመት የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር ተማሪዎችን በስነ ልቦና ዝግጁ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቢሮው ከ2015 አፈጻጸም በመነሳት የስድስተኛ ክፍል ውጤት ጠንካራ እና የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እንደነበር መገምገሙን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ተማሪዎች ኩረጃ የተከለከለ መሆኑን በማወቅ በስነ ልቦና መዘጋጀት፣ መረጋጋትና ሙሉ ትኩረታቸውን ፈተናው ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ነው ዳይሬክተሩ ያሳሰቡት።
ከተማ አቀፍ ፈተናው በተለይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከምዝገባ ሂደት ጀምሮ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸው ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው ከመምህራን ማህበር ፤ጤና ቢሮ ፤ፖሊስ ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከምገባ ኤጀንሲ ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ ፤ለጸጥታ አካላት በቂ ገለፃ በመስጠት ጸጥታውን የማስከበር ስራ እንዲሰሩ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ከተፈቀዱ የፈተና ቁሳቁሶች ውጭ ሌላ መገልገያ ይዞ ወደ ፈተና መግባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ዲጂታል ሰዓትን ጨምሮ ማንኛውንም ኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን እና ቀሳቁሶችን ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በፈተና ወቅት ማንኛውም አይነት የጤና ችግር ቢያጋጥማቸው የህክምና እርዳታ የሚያደርጉ የጤና ባለሙያዎች በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች መመደባቸውንም በማስታወቅ ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናውን እንዲሰሩ አሳስበዋል።