ቀጥታ፡

የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ሁሉም በጠንካራ የሃላፊነት ስሜት ሊሰራ ይገባል

ጂንካ፤ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ስብራት በመጠገን ለውጤታማነቱ  መስራት የሁሉንም ቁጭትና ጠንካራ ሃላፊነትን ይጠይቃል  ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለፁ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2016 ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማና የቀጣይ ወራት ዕቅድ ላይ የሚመክር ጉባዔ በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ በገጠመን የትምህርት ስብራት በተማሪዎች ውጤት ላይ ማሽቆልቆል ታይቷል።

መንግሥት ይህንን ችግር ለመሻገር የሚያስችሉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችንም እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ለሪፎርም ስራው ውጤታማነት የሁሉም ድጋፍ እና እገዛ ያሻል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ''ላጋጠመን የትምህርት ስብራት ችግር ምክንያት ከመደርደር ወጥተን ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመሻገር መስራት ይኖርብናል'' ብለዋል።

በትምሀርት ውጤት ላይ ለታየው ድክመት ተማሪዎች፣ የፖለቲካ አመራሩ፣የትምህርት ባለሙያዎችና ወላጆች ራሳቸውን በመጠየቅ ለመፍትሄው በአንድነት ሊሰለፉ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።


 

የአንድ ሀገር ልማትና እድገት መሠረቱ ትምህርት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም ሰው ለትምህርት ጥራት መጠበቅ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የትምህርት መሰረተ ልማትን በሟሟላት ትምህርት ቤቶችን የማገዝ ስራ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጉባኤው “በአዲሱ ክልል በአዲስ ዕይታና በአዲስ አስተሳሰብ የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ለትምህርት ጥራት''በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።

ለአንድ ቀን በተሰናዳው በዚሁ መድረክ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና የዞን የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም