ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ 14 ስምምነቶችን ተፈራርመዋል- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር 14 ስምምነቶች መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ቻይና ቤጂንግ  መግባታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና ከሚያደርጉት የስራ ጉብኝት ጎን ለጎን ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር በሚያጠናክሩባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴአታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደተናገሩት ሁለቱ ሀገራት 14 የትብብር ስምምነቶችን የተፈራረሙ ሲሆን ስምምነቶቹ በአራት ዘርፎች የተከፈሉ ናቸው።

እነዚህም የስምምነት ሰነድ፣ የፕሮቶኮል፣ የደብዳቤዎች ልውውጥና ከዚህ ቀደም የተፈረሙ የመግባቢያ ሰነዶችን መተግበሪያን የተመለከተ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ስምምነቶቹ በግብርና ልማት፣ በአርንጓዴ ኢኮኖሚና በከተማ ልማት፣ መሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያ እንዲሁም የቤልት አንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ እንዴት ይተገበራል የሚለውን ያቀፉ ናቸውም ነው ያሉት።


 

የቁሳቁስና የሰው ሀብት ልማት ድጋፍ፣ የባህልና ቱሪዝም ትብብር እንዲሁም በጤናው ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉና ፈርጀ ብዙ ጉዳዮችን ያቀፉ ጉዳዮች ላይ የስምምነት ፊርማ ተካሂዷል ሲሉም ገልጸዋል።

እነዚህ ስምምነቶች የሀገራቱን ተጠቃሚነት በማሳደግ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ መሆናቸውን ያብራሩት አምባሳደር ብርቱካን ስምምነቶቹ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም