ቀጥታ፡

የአፋርን እምቅ የባህል ሀብቶች አጉልቶ ለማውጣትና ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሰራ ነው-የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

ሰመራ፤መስከረም 23/2016(ኢዜአ)፡- የአፋርን እምቅ የባህል ሀብቶች አጉልቶ ለማውጣትና ለማስተዋወቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የዓለም የቱሪዝም ቀን በአፋር ክልል ደረጃ በፈንቲ ራሱ ዞን በተለያዩ ዝግጅቶችና ትዕይንቶች ታጅቦ "ቱሪዝም ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንት "በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

በበዓሉ የጉሊና፣አውራ፣እዋ፣ያሎና ቴሩ ወረዳዎች የባህል ቡድኖቻቸው ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን አቅርበዋል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ አህመድ አብዱልቃድር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ቢሮው ያልተጠኑ፣ ያልታወቁና ያልታዩ ባህሎችን አጎልቶ በማውጣትና በማስተዋወቅ በትኩረት እየሰራ ነው።

ባለፉት ወራት የክልሉን የባህል ሀብቶች በመለየት ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ እየተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል።

ዞኑ መሳጭ ባህላዊ ጭፈራዎች ያሉት በመሆኑ ባህሉን ለማስተዋወቅ መመረጡን ገልጸዋል።


 

በዓሉም የክልሉን ቱባ ባህል ለማስተዋወቅና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱንም አቶ አህመድ አስረድተዋል።

በዓሉ የክልሉን የቱሪስት መስህቦች ከማስተዋወቅ ባሻገር፤ክልሉን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ቁጥር ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ አካላትም የሚመሰገኑበት ነው ብለዋል።

በዞኑ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማጠናከር ሰላም፣ልማትና የህዝቦች አንድነትን ማጠናከር እንደሚያሻም ኃላፊው አመልክተዋል።

የፈንቲ ረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢላል ደርጌ በበኩላቸው በዓሉ በዞኑ መከበሩ የክልሉን ቅርሶችና ታሪክ በስፋት ለማስተዋወቅ፣ተገቢው ጥበቃ ለማድረግና ለቀጣይ ትውልዶች ለማስተላለፍ ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።


 

"ድባቡ በጣም ደስ የሚል ነበር፤ቱባ የሆኑትን ባህሎች ያየንበት ነበር" በማለት የተናገሩት ደግሞ የጉሊና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ ኢብራሂም ናቸው።

ከሁሉም ወረዳዎች ተወጣጥተው በመምጣት ባህላዊ ጭፈራዎች፣ የምግብ ዓይነቶችና የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ ከክልሉ፣ ከዞኖችንና ወረዳዎች የተውጣጡ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

 
 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም