በመዲናዋ ከሁለት መቶ በላይ ሆቴሎችና የምሽት መዝናኛ ቤቶች ከተፈቀደላቸው በላይ ድምጽ በመጠቀማቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል - የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን

185

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከሁለት መቶ በላይ ሆቴሎችና የምሽት መዝናኛ ቤቶች ከተፈቀደላቸው በላይ ድምጽ በመጠቀማቸው እርምጃ መውስዱን የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ። 

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ድዳ ድሪባ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት ከ400 በላይ ሆቴሎችና የምሽት መዝናኛ ቤቶች ላይ የቁጥጥር ሥራ ተሰርቷል። 

ለዚህም የድምጽ መለኪያ መሳሪያ ሥራ ላይ በማዋልና በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ የድምጽ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉን ነው የገለጹት።      

በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ሆቴሎችና የምሽት መዝናኛ ቤቶች የነዋሪውን ጸጥታና ምቾት የሚነሱ መሆናቸውን እንደተደረሰባቸው ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣኑ በ208 ሆቴሎችና የምሽት መዝናኛ ቤቶች ከተፈቀደላቸው ድምጽ በላይ በመጠቀማቸው የተለያዩ እርምጃ እንደወሰደባቸው ተናግረዋል። 

እርምጃዎቹ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ማሸገ የሚደርስ መሆኑን ጠቁመው ባለሥልጣኑ በእነዚህ የመዝናኛ ቤቶች የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሆቴሎችና በምሽት መዝናኛ ቤቶች ሕግና ደንብን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የጠየቁት ሥራ አስኪያጁ ከተማዋ ለነዋሪዎች ምቹ እንድትሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም