የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ ነው - የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 

271

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2015 (ኢዜአ)  የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።     

የኮርፕሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ መምሪያ ኃላፊ ዘመን ጁነዲ ኮርፖሬሽኑ የአገሪቱን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ከመስራት ጎን ለጎን ለአካባቢ ጥበቃና ሥነ-ምህዳር መጠበቅ የራሱን አበርክቶ እየተወጣ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከ2 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።  

ችግኞቹ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ሲደረግላቸው የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ የፅድቀት መጠናቸውም ከ90 በመቶ በላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ1 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከርና ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት። 


 

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋይናንስና አስተዳደር አገልግሎት ኃላፊ ሲሳይ አስፋው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተቋማትን በአረንጓዴ ዕጽዋቶች በማስዋብ ጽዱና ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። 

መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ሰራተኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከልና በመንከባከብ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

በ5ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፈሳሽ ማጣሪያ አስተባባሪ ሰይፈ ፈረደ በበኩላቸው ከፋብሪካው የሚወጣው የታከመ ውሃና የደረቅ ቆሻሻ ብስባሽ ለሚተከሉት ችግኞች ህይወት መስጠቱን ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ደግሞ ከ7 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም