ባለሀብቶች በወልዲያ ያለውን ምቹ ልማት አቅም ተጠቅመው መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ አለባቸው -  አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ 

167

ወልዲያ ፤ መጋቢት 16 ቀን 2015 9ኢዜአ) ፡ ባለሀብቶች በወልዲያ ያሉ እምቅ የልማት አማራጮችን በመጠቀም መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ  አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ጥሪ አቀረበ።

አትሌት  ኃይሌ ከወልዲያ አመራሮችና ነዋሪዎች ጋር በመሆን ከተማዋንና የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም ጎብኝቷል።

አትሌት ኃይሌ "ወልዲያ ከተማ በአራቱም አቅጣጫ የተለያዩ የሀገራችንን ክፍሎችና ከጅቡቲ ወደብ የሚያገናኙ መንገዶች ያሏት መሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል" ብሏል።

ከዚህም ሌላ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ መሆኗ ለዘርፈ ብዙ ልማት ምቹ ሁኔታዎች እንዳላት መረዳቱን ገልጿል።

ይህን ምቹ አጋጣሚና ወርቃማ እድል በመጠቀም በተለይ ባለሃብቶች በከተማዋ መዋዕለ-ንዋያቸውን ተጠቅመው ሊለሙ እንደሚገባ አመልክቷል።

''እኔ በጥናት ወደ ወልዲያ መጥቻለሁ ሌሎች ባለሃብቶችም ለጋራ ልማት ኑ፤ ወልዲያን  በጋራ እንልማ'' ሲል ተናግሯል።

ከፍተኛ ሃብት የፈሰሰበትና ትልቅ የሃአር ሃብት የሆነው የሼህ ሙሐመድ አሊ አልአሙዲ ስታዲየምን ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባም  ጠቅሷል።

ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ባለ ስምንት መሮጫ ትራክ ያለው፣ ደረጃውን የጠበቀ ወንበር የተሟላለት ጣሪያውና ሌሎችንም መመዘኛዎች ያካተተ ነው። 

በዚህ ስታዲየም በቅርቡ የሩጫ ውድድር በማካሄድ ከተማዋን የማነቃቃት ስራ ይከናወናል ነው ያለው አትሌት ሻለቃ  ኃይሌ ገብረ ስላሴ።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ፤  ዝነኛው አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ የወልዲያ ከተማን የመጎብኘት ጥሪ ተቀብሎ በመምጣቱ ምስጋናቸወን አቅርበዋል።

''ኃይሌ የአገራችን ጀግና አትሌት ብቻ ሳይሆን ሃብቱን ለሃገር ልማት ያዋለ ባለውለታ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ያቀረበለትን የአብረን እናልማ ጥያቄ ተቀብሎ ዛሬ መገኘቱ የልማት ስራው አንድ እርምጃ እንደሆነና ለኢንቨስትመንት አመቺ ቦታዎችን በአማራጭነት ለመስጠት አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ባቀረበው ጥሪ መሰረት 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው ባለሃብቶች ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ ለእነዚህም ከተማ አስተዳደሩ አዎንታዊ መልስ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በጉብኝቱ ላይ የሰሜን ወሎ ዞን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤርሚያስ ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አመራሮችና ሌሎችም ነዋሪዎች  ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም