በአዲስ አበባ ከ150 ሺህ በላይ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሚኒስትሪ ለመፈተን ተመዝግበዋል- ትምህርት ቢሮ

404

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዘንድሮ ከ150 ሺህ በላይ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሚኒስትሪ ለመፈተን መመዝገባቸውን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። 

በአዲሱ ስርአተ ትምህርት መሰረት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚኒስትሪ ፈተና እንደሚወስዱ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳኛው ገብሩ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት በመዲናዋ ዘንድሮ ከ150 ሺህ በላይ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሚኒስትሪ ለመፈተን ተመዝግበዋል።

ለተፈታኞቹ 368 የፈተና መስጫ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ኩረጃን በመጸየፍ በራስ አቅም ውጤት ማምጣት የሚችል ትውልድ ለማፍራትም ለተፈታኝ ተማሪዎች አስፈላጊው የእውቀት እና በስነልቦና ግንባታ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

መምህራኑም ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በእውቀትና በስነ-ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ከመማሪያ ከግብአት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የተወሰኑ መጻሕፍት ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የደረሱ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ዳኛው ያመለከቱት።
 
ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የማካካሻ ትምህርት በመውሰድ ለፈተናው የበኩላቸውን ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኝ ተማሪዎች፣መምህራንና የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ገልጸዋል።
 
ለአዲስ አበባ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ የሚኒስትሪ ፈተና ከሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በኋላ ባሉት ቀናቶች እንዲፈተኑ እቅድ መያዙን ከከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም