ሁለተኛው ምዕራፍ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዝግጅት በመገባደድ ላይ ነው  - የገንዘብ ሚኒስቴር 

188

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦  ሁለተኛው ምዕራፍ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዝግጅት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ። 

ማሻሻያውን አስመልክቶ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተለይም የኢኮኖሚ እድገቱን የተሳለጠ ለማድረግ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸው ይታወቃል።

የኢኮኖሚውን እድገት ለማስቀጠል የሚያስችል ተጨማሪ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግና ለዚህም ሁለተኛው ምዕራፍ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ማሻሻያው የመልሶ ግንባታ ስራን ለማሳለጥና የማክሮ ኢኮኖሚውን ክፍተት በማጥበብ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአገር ውስጥና በውጫዊ ምክንያቶች በኢኮኖሚው ላይ የተፈጠረውን ጫና ለመቀነስም የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዝግጅት እየተገባደደ እንደሚገኝና በማሻሻያው ላይ በቀጣይ ከልማት አጋሮች ጋር ውይይት እንደሚደርግም ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።

በሌላ በኩል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ የተፈጠረውን ጫና መቋቋም የሚያስችል የማሻሻያ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ጫናውን በመቋቋም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሬ አቅምን ለማሻሻልና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው የፖሊሲ እርምጃ እንደሚወሰድ አመልክተዋል።

በዘላቂ የፋይናንስ መርህ ላይ ተመስርቶ በቁልፍ የመሰረተ ልማት ግንባታና በከተማና ገጠር ሴፍቲኔት መርሐግብር መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን ለመቻል በስንዴ፣ በቆሎ እና በሌሎች የሰብል ምርታማነት ላይ የተገኘውን ውጤት የበለጠ እንዲጠናከር ይሰራል ያሉት አቶ አህመድ የግብርና ምርቶች ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጪ ገበያ የማዋል ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ያለባትን የእዳ ጫና ወደ መካከለኛ ደረጃ እንዲወርድ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን ማሻሻል የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ እንደሚወሰድም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም