የኦሮሚያ ክልል የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ ነው -- አቶ አወሉ አብዲ

482

አዳማ ኢዜአ መጋቢት 15/2015፡- የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለፁ።

የ2015/16 ዓ.ም የመኸር አዝመራ ዝግጅት እንዲሁም የክልሉ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ አባገዳ አደራሽ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚሁ ጊዜ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ እንደገለፁት የክልሉን ህዝብ ህይወት ማሻሻል በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት ተድርጎ እየተሰራ ነው።

አርሶ አደሩ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት እንዲኖረውና ከባንክ ጭምር የብድር አገልግሎት የሚያገኝበትን ዘመናዊ ቤት እንዲኖረው ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ዛሬ በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ አማካኝነት 100 ሺህ ዘመናዊ የገጠር መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት መታቀዱንም ተናግረዋ።

ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶቹ ከአካባቢው በሚገኙ ቁሳቁሶች በአነስተኛ ዋጋ የሚገነቡ መሆናቸውን አመልክቷል።

በሌላ በኩል ዘንድሮ በክልሉ ቡሳ ጎኖፋ አማካይነት ከ5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በተያያዘም በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው በየደረጃው ያለው አመራርና የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም አቅርበዋል።

በክልሉ ህገ ወጥ የእህል ንግድ፣ የማዕድንና የእንስሳት ሀብት ንግድ፣ ኮንትሮባንድ ከፍተኛ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም