የሚሰበሰበውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓትን ማጠናከር ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

260

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦ የሚሰበሰበውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር "ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ሃሳብ የታክስ ህግ ተገዥነት የንቅናቄ ማስጀመሪያና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ-ግብር በሳይንስ ሙዚየም ዛሬ አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ በ2014 የግብር ዘመን የሚጠበቅባቸውን የግብር ግዴታ በታማኝነትና በወቅቱ ለተወጡ 300 ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አዲስ አበባ አስፈላጊው መሰረተ ልማት ተሟልቶላት ለዜጎች ምቹ እንድትሆን ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ ነው።


 

ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ ደግሞ ከብልሹ አሰራር የጸዳ ዘመናዊ የግብር አሰራር ሥርዓት መዘርጋትና የተጀመሩትን ዘመናዊ አሰራሮች ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ግብር መክፈል ግዴታ መሆኑን ተረድተው ግብርን የሚከፍሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ተናግረው በጎ ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


 

በሌላ በኩል ከግብር ሥርዓቱ ውጪ የሆኑ አካላት ወደ ግብር ሥርዓቱ መካተት እንዳለባቸው ተናግረው ግብር በመክፈል የዜግነት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የታክስ አሰባሰብ ሂደቱ ሁሉንም ያቀፈና ውጤታማ እንዲሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሊጠናከሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በመድረኩ የግብር ግዴታቸውን በአግባቡ ለተወጡ 300 ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም