በመኸር ወቅት ከ151ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ የእርሻ ስራ ተጀምሯል-የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ

276

ጋምቤላ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በተያዘው መኸር ወቅት 151ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ  የእርሻ ስራ መጀመሩን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በመኽር ወቅት በሰብል ለማልማት ከታቀደው መሬት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢሮው አመላክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደገለጹት አሁን ላይ በምግብ ፍጆታ ምርቶች ላይ እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ጫና ለማርገብ በተያዘው የመኸር እርሻ ምርታማነትን ለማሳዳግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

አሁን ላይ የተከሰተውን የኑሮ ጫና ለማርገብ የሁሉንም ተሳተፎ በማጎልባት የግብርና ልማትን ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በክልሉ 2015/16 ምርት ዘመን መኽር ወቅት 151 ሺህ 971 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የተሰራ መሆኑን አቶ አጃክ አመላክተዋል።

በምርት ወቅቱ ለማለማት የታቀደው መሬት ከባለፈው ተመሳሳይ ምርት ወቅት ከለማው ጋር ሲነፃፀር 20 ሺህ ሄክታር ብልጫ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ለመሰብሰብ የታቀደው የምርት መጠንም 670ሺህ ኩንታል በላይ ብላጫ እንደሚኖረው አመላክተዋል።

ቢሮው ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ 4ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ፣ የማሽላ፣ የሰሊጥ፣ የሩዝና ሌሎች የምርጥ ዘር ግብዓቶች በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለመኽር ወቅት እርሻው እየተደረገ ካለው ዝግጅት ጎን ለጎን በልግ አብቃይ በሆነው የማጃንግ ዞንም የምርጥ ዘር ስርጭት መካሄዱን ተናግረዋል።

በተሻሻሉ የግብርና መሳሪያዎችና የአሰራር ዘዴ አርሶ አደሩን በመደገፍ የእርሻ ልማቱን ለማስፋፋት ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በድጋፍ የተገኙ 36 የእርሻ ትራክተሮች ወደ ወረዳዎች እንዲሰራጩ መደረጉን አቶ አጃክ አስታውቀዋል።


 

እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የባለሙያዎችና የከፍተኛ አመራሮች ስምሪት ተደረጎ በእቅዱ ላይ ውይይት በማድረግ የተጠናከረ የንቅናቄና የማሳ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ አጃክ ተናግረዋል።


 

በዘርፉ እየተካሄደ ባለው ንቅናቄ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት አመራሮች መካከል የአኝዋሃ ዞን አስተዳደሪ አቶ ኡቦንግ ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት የዘንደሮውን የመኸር እርሻ ዝግጅት ባለሙያዎችና በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትን በማሰማራት በወቅቱ መጀመሩን ገልጸዋል።

"አሁን ላይ የክልል አመራሩና ባለሙያዎች በተጨማሪ ወደ ዞኑ በመምጣት የተጠናከረ የንቅናቄና የማሳ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል።


 

በአኝዋ ዞን አበቦ ወረዳ በዋንኮክ ቀበሌ የማሳ ዝግጅት እያደረጉ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል አሪያት ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት ቀድሞ ለሚዘራ የቆሎ ሰብል የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"አሁን ላይ የተፈጠረውን የኑሮ ችግር ማሸነፍ የሚቻለው የግብርና ስራን ጠንክሮ በመስራት ነው፤ ስለዚህም ከኑሮ ጫናው ለመውጣት እየሰራሁ ነው" ብለዋል።


 

አሁን ላይ ለመኸር እርሻ የማሳ ዝግጅት የምንጣሮ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ተስፋዬ ኡላሞ ነው።

በወቅቱ ወደ ግብርና ልማቱ በመግባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማሸነፍ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

በጋምቤላ ክልል ባለፈው የመኸር ወቅት እርሻ 131ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች መልማቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም