በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያመጡ መሆኑ ተገለፀ

266

ድሬዳዋ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችና የጎርፍ መከላከያ ግንቦች አበረታች ውጤት ማምጣታቸውን በአስተዳደሩ የመንግስታዊ ተቋማት አመራሮች እና ነዋሪዎች ገለጹ።

የድሬዳዋ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ እየጣለ ባለው ዝናብ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።


 

የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ወርቅነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ባለፉት 10 ዓመታት የተገነቡ የጎርፍ መከላከያ ግንቦች የጎርፍ አደጋን በከፍተኛ ደረጃ ለመከላከል አስችለዋል።

ጎርፍ በተደጋጋሚ ጊዜ በሰውና በንብረት ላይ ጥፋት ሲያደርስባቸው በነበሩ የደቻቱ እና የቡቲጂ ወንዞች ግራና ቀኝ የተገነቡ ግንቦች ችግሩን በመከላከል በኩል መሠረታዊ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።


 

ዘንድሮም በመልካ ጀብዱ ቀበሌ 100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው እየተጠናቀቁ ያሉ ግንቦች የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ተናግረዋል።

እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ተከትሎ ጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት በገጠርና በከተማ የጎርፍ መውረጃዎችን የማስተካከልና የፈረሱ ግንቦችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ብሩክ ተናግረዋል።


 

የድሬዳዋ የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በገጠር ቀበሌዎች የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች በከተማና በገጠር ይደረስ የነበረን የጎርፍ አደጋ በመሠረታዊነት መከላከል አስችለዋል።

በገጠር የተከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃና ልማት ሥራ የጎርፍ ውሃን ወደ መሬት በማስረግ በከርሰ ምድር ውሃ የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ እያገዘ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት ጎርፍ የእርሻ መሬትን ጠራርጎ ወደ ከተማው በማስገባት ችግር ይፈጥር እንደነበር አስታውሰው፣ "አሁን ግን የጎርፍ ውሃን ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል" ብለዋል።


 

ድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች አንዷ መሆኗን የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም ዩሱፍ ናቸው።

የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የተሰሩ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም አሁን እየጣለ ባለው ዝናብ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡን የማስጠንቀቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ በተራራማ ስፍራዎች ላይ እና በጎርፍ መውረጃ ቦዮች ላይ ቤት ገንብተው የሚኖሩ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።


 

የዋሂል ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር አብደላ ዑስማን ከስድስት ዓመታት በፊት ጎርፍ የእርሻ ማሳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለፉት ዓመታት በገጠሩ ህብረተሰብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተሰሩ የተፋሰስ ልማቶች ችግሩ እንዲቀንስ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

የተሰሩት የድንጋይ ክትሮች የጎርፍ ውሃን ለጥቅም ለማዋል ከማስቻላቸው ባለፈ የምንጭ ውሃ ጎልብቶ  ኑሯቸውን በመስኖ ለማሻሻል እንዳገዛቸው ገልጸዋል።


 

"በደቻቱ ወንዝ ላይ የተገነባው ግንብ ህብረተሰቡን ከጎርፍ አደጋ እየታደገ ይገኛል" ያሉት ደግሞ በድሬደዋ "አሸዋ" በሚባለው አካባቢ የሚኖሩት አቶ ፀጋዬ ንጋቱ ናቸው።

በመልካ ጀብዱ ቀበሌ አካባቢ እየተገነባ ያለው የጎርፍ መከላከያ ግንብ የአካባቢውን ህብረተሰብ ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ጁኔይዲ ኢብራሂም ነው።

ሐምሌ 28/1998 ከእኩለ ለሊት ጀምሮ በድሬዳዋና ተጎራባች ወረዳዎች የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በሌሊት የመጣው ጎርፍ 250 ሰዎችን ሲገድል፤ 10ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ያለመጠለያ ማስቀረቱ ይታወሳል።

በወቅቱ ጎርፉ 10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት መሠረተ ልማቶችን በማውደሙ "የድሬዳዋ ጥቁር ቀን" በሚል እንደሚዘከር ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም