በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቃዮችን ከማቋቋም ባለፈ ሥነ ልቦናቸውን ማጎልበት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል--የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ

207

አሶሳ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ከማቋቋም በተጓዳኝ ሥነ ልቦና ማጎልበት ስራም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ነው ቢሮ የጠየቀው

በክልሉ ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ተፈናቃይ ወገኖች ምላሽ መስጠትን ያለመ ስልጠና ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አበራሽ ደጃስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ጥረቱ እንደቀጠለ ነው።

በተለይ ሴቶችና ህጻናት የችግሩ ዋነኛ ተጠቂ መሆናቸውን ጠቁመው፤ "ከመልሶ ማቋቋም ሥራው በተጓዳኝ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።

በመሆኑም ባለድርሻ አካላት ከሚያደርጉት ሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ ተከታታይነት ያለው የሥነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያደርጉ ወይዘሮ አበራሽ ጠይቀዋል።


 

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር ድጋፍ የማድረጉ ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠውም ጠቁመዋል።

"በክልሉ በነበረው የሰላም እጦት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም እርስ በርስ መደጋገፍን ማጠንከር ይገባል" ሲሉም ምከተል ቢሮ ሀላፊዋ ገልጸዋል

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ያረጋል ፉፋ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ መንግስታዊ ተቋማትን አንዲሁም በሥነ ልቦናና ማህበራዊ ዘርፍ የሚሰሩ ማህበራትን በማስተባበር የጤናና የስነ-ልቦና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንጻር ሲታይ አሁንም በርካታ ቀሪ ሥራዎች አሉ ብለዋል

ሰልጠኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል የሚያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች በማስተላለፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ስልጠናው በዋናነት በጤና፣ በሥነ-ልቦናና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰጥ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የሚኖሩ 300 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም