ኢትዮጵያና አሜሪካ ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - አሜሪካውያን ተንታኞች

385

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና አሜሪካ ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሜሪካውያን የመስኩ ተንታኞች ገለጹ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ ኢዜአ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማንና ከአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ተንታኙ ከጋዜጠኛ ጆሴፍ ሃሞንድ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ተንታኞቹ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ስትራቴጂክ አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ አሜሪካም ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዲኖራት መሥራት እንዳለባት ጠቅሰዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በአፍርካ ቀንድ ተፅዕኖ ካላት ኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ያሳየ ነው ይላሉ።

ላውረንስ ፍሪማን እንደሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ የወሰደችው ቁልፍ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ነው።

አሜሪካ በአፍሪካ ተፅዕኖ መፍጠር እንደምትፈልግ ቢታወቅም የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት ግን ከዚያም ያለፈ ነው ይላሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን።

አሜሪካ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ አጋርነቷን ማሳየቷን ጠቅሰው፤ የአሜሪካ መንግሥት ከዚህም ባለፈ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ ልማት ጠንካራ ትብብር ሊፈጥር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሁለቱ አገራት ሁሉን አቀፍ ጠንካራ ወዳጅነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያነሱት ላውረንስ፤ በዚህም ሰፋፊ መሰረተ ልማቶችን የመዘርጋት፣ የልማት ፕሮግራሞችን የመተግበር ትብብር ይጠናከራል ብለዋል።

አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እንዲሁም በአፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ለማጠናከር ከእርዳታ ይልቅ ሰፋፊ የኢኮኖሚ ድጋፎችን ማድረግ ላይ ማተኮር እንዳለባትም ጠቅሰዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በአህጉሪቱና በቀጣናው ያላትን የህዝብ፣ የጂኦ-ፖለቲካ አቀማመጥና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ በአግባቡ መገንዘብ እንደሚገባ በመጠቆም።


 

የሰላምና ሚዲያ ኢኒሼቲቭስ ማዕከል ባልደረባ እና የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ተንታኙ ጋዜጠኛ ጆሴፍ ሃሞንድ በበኩላቸው፤ የብሊንከን ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል መልካም ግንኙነትን የማደስ የመጀመሪያው ጡብ ነው ብለዋል።

አክለውም ጉብኝቱ የሁለቱ አገራት የተቀዛቀዘ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ፍላጎት ላላቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ትልቅ ድል መሆኑን አክለዋል።

የባይደን አስተዳደር በአፍሪካ መልካም ግንኙነትን ለማጠናከር በአህጉሪቱ ውስጥ ስትራቴጂክ አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን በቀዳሚነት ማሳተፍና ጠንካራ ትብብርን መፍጠር እንዳለበት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም