የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር መግባባት የተፈጠረበት ነው

307

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015(ኢዜአ)፦የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅታዊና አገራዊ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር መግባባት የተፈጠረበት መሆኑን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ለቀጣይ ስራዎች መግባባት የተፈጠረበት መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

በስብሰባውም የተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሻገር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መግባባት ላይ የተደረሰበት ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ እንዳሉት፤ በተለያዩ አካላት የሚፈጠሩ አፍራሽ አጀንዳዎች ኢትዮጵያዊያንን እየፈተኑ መሆኑን በስራ አስፈጻሚው በጥልቀት ተገምግሟል ብለዋል፡፡

በተለይ ነጻነትን በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻል ምክንያት የተለያዩ አካላት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ጭምር ለዘመናት የተገነባውን የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም በቀጣይ አብሮነታችንን በማጠናከር ይህንን ችግር ለማረም በትኩረት መስራት እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ረገድ በየደረጃው ያለው አመራር የህዝቦችን አብሮነት የማስጠበቁን ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት መስራት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡


 

ሌላኛው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ግርማ የሺጥላ የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ያልተጠናቀቀ የቤት ስራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይ በታሪክና ትርክት ህዝብን ለመለያየት የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ህዝብን የመለያየት አጀንዳዎች አገር ውስጥ ባሉ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህልውና የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር ጭምር በትብብር የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ህዝብን በማሳተፍ በየደረጃው ያሉ ወቅታዊና አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል፡፡

እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድና ህዝብን በማወያየት በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡


 

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው ጽንፈኝነት የወቅቱ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን አፍራሽ አካሄድ በመታገል የተጀመሩ የልማት መንገዶችን ማስቀጠል እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የፍትህና ጸጥታ ተቋማትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ወቅታዊ የኑሮ ውድነት ፈተናዎችን መፍታት ላይ በትኩረት መወያየቱም ተጠቁሟል፡፡


 

የምርት እጥረት ሳይኖር የዋጋ ንረት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ነው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል ሞገስ ባልቻ የተናገሩት፡፡


 

ሌላኛው የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘላለም ከበደ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰራጩ አፍራሽ አጀንዳዎች በህዝብ ላይ ተጽእኖ እንዲፈጥሩ መፍቀድ እንደማይገባ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በየደረጃው ያሉ አመራሮች የህዝብን አብሮነት በማጠናከር በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን ለህዝብ ጥቅም ለማዋል በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም