ቀጥታ፡

ሀገራዊ የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

ሀዋሳ ሐምሌ 13/2012(ኢዜአ ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የህዝብን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ እየመለሰ ያለው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ፡፡ 

በወቅታዊ ሃገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ለሶስት ቀናት የተዘጋጀ የደቡብ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ኮንፍረንስ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በኮንፍራንሱ መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት አቶ ርስቱ  እንዳስታወቁት በህዝቦች ግፊት ዕውን የሆነው የለውጥ ጉዞ ሃገሪቱ ከተጋረጠባት አደጋ ሊታደጋት ችሏል፡፡

ይህም ለውጡ ሠላማዊ በሆነ አካሄድ እንዲጓዝና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ለረጅም ዘመናት አብሮን የቆዩ ስህተቶች ለማረም መንግስት በወሰዳቸው ቁርጠኛ አቋም በመላው አፍሪካና ሌላውም ዓለም የሚያኮሩና አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በለውጡ ሂደት በተካሄደው ሁለንተናዊ ሪፎርም  ህዝቡን ያማረሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች በመንግስትና ህብረሰተቡ መካከል ፈጥረው የነበሩትን መራራቅ ማረም መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ለውጥ ያስፈለገው በፊት የተዛነፉና ኢ-ፍትሐዊ የነበሩ አሠራሮችን ለማረም ነው ያሉት አቶ ርስቱ ለውጡ ይመጣብናል ያሉ ኃይሎች ሂደቱን ለማደናቀፍና ህዝቡን  መልሶ ለመከራ ለመዳረግ የሚችሉትን ሁሉ ሴራ በመሸርብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህም ከውስጥና ውጭ ከህዝብ ይልቅ ለግል ጥቅማቸው የሚታትሩ ቡድኖች በማበጀት የሚሰሩ መሆናቸውን አመልከተው አሁን ላይ የክልሉ መንግስት ለመፍታት የጀመረውን የአደረጃጀት ጥያቄ ሌላ መልክ ለማስያዝ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በተገቢው አለመስራታቸው እንደሆነ ጠቁመው ኮንፍራንሱ ይህንን ለማስተካከል በአመለካከትም ሆነ በተግባር የተዋሄደ የአመራር ቁመና ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ርስቱ ሃገራዊ የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በየደረጃው የሚገኘው አመራር በብቃትና ቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ ከውስጥና ውጪ ከፍተኛ ሴራ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው።

አመራሩ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ እንዲሁም የክፉዎችን ሴራ ለማክሸፍ በከፍተኛ ትኩረት አንድነቱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ኮንፍረንሱ በቆይታው ሃገራዊና ክልላዊ ቀጣይ የልማት፣ ጸጥታ እና በክልሉ የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች በተመለከተ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም