በሰሜን ወሎ ዞን ገበያን የማረጋጋት ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ወሎ ዞን ገበያን የማረጋጋት ስራ እየተካሄደ ነው
መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም (ኢዜአ) በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኔኖች እየተካሄደ ያለው ገበያ የማረጋጋት ስራ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በወልድያ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ገለጹ። የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከ30 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን የሰሜን ወሎ ዞን ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል። በከተማው የቀበሌ ሶስት ነዋሪ ወይዘሮ ዘነበች መንገሻ ለኢዜአ እንደገለጹት አሁን ላይ በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ከአቅማቸው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ''በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ሰሞኑን ጤፍን ጨምሮ እየቀረበ ያለው ሸቀጣ ሸቀጥ ምርት ተጠቃሚ እያደረገን ነው'' ብለዋል፡፡ ሰሞኑንም ከነጋዴው ከ2ሺህ 800 ብር በላይ የሚሸጥ አንድ ኩንታል ጤፍ ከጀምበር ዩኒየን በ2 ሺህ 400 ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም 280 ብር የሚሸጥ አስር ኪሎ የፍርኖ ዱቄት በ88 ብር በመግዛት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልዋል። በወልድያ ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይ ምረቴ በበኩላቸው ዩኔኖችና ማህበራት የምግብ እህል፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ አትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች ሸቀጦችን በማቅረብ ገበያውን እያረጋጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ነጋዴው የሚያቀርበው ጤፍ ዋጋ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ቀላቅለው ስለሚሸጡ የጥራ ደረጃው አሳሳቢ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። በወልድያ ከተማ የመምህራን ሸማቾች ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ገበያው ዘገየ በሰጡት አስተያየት ባለፈው ወር መጨረሻ ከመንግስት በተሰጣቸው አንድ ሚሊዮን ብር ብድር የገበያ ማረጋት ስራ ሰርተዋል። በተደረላቸው ድጋፍ የካፒታል አቅማቸው እየተጠናከረ በመምጣቱ ከምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል። በሰሜን ወሎ ዞን የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ ተከታይ ደሴ እንደገለጹት የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከ30 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህንኑ ገንዘብም ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በብድር በመስጠት ከሌሎች አካባቢዎች ምርቶችን ገዝተው ለሸማቾች እንዲያከፋፍሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዩኔኖቹ ከ4 ሺህ 600 ኩንታል በላይ ጤፍና በቆሎ በማስመጣት ነጋዴው ከሚሸጥበት ዋጋ በኩታል በ500 ብር ቀንሰው በማከፋፈል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው፡፡ በዞኑ በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች ችግሩ ተባብሶ እንዳይቀጥል የገበያ አረጋጊ ግብረሃይልና የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡ ግብረ ሃይሉ ከነሀሴ 29 እስከ ጳጉሜን ሶስት ቀን 2009 ዓ.ም በአንዳንድ ከተሞች ባካሄደው የቁጥጥር ዘመቻ ያለ ንግድ ፈቃድ ሲሰሩ በተገኙ 606 ነጋዴዎች ላይ ማስጠንቀቂያና የንግድ ቤታቸው ታሽጎ ፈቃድ እዲያወጡ ተደርጓል። በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ ተከዝኖ የተገኘ 500 ኩንታል ስኳር 598 ሊትር ዘይት ተወርሶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ መደረጉን ገልጸዋል። በቀጣይም ሸማቾች ማህበራትንና ዩኒየኖችን በካፒታል በማጠናከርና ህገወጥ ንግድን በመቆጣጠር የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋት እንዲሁም ህበረሰቡ የራሱን መብት እንዲያስከብር ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።