ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል አዲሱ የወረዳዎች አደረጃጀት የህዝብን ብዛት፣ ፍላጎትና የቦታ ርቀት ያገናዘበ አይደለም...የህዝብ ተወካዮች

ማይጨው (ኢዜአ) ነሃሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም---በትግራይ ክልል አዲስ ተጠንቶ የቀረበው የወረዳዎች አደራጃጀት የህዝብን ብዛት፣ ፍላጎትና የቦታ ርቀትን ያገናዘበ አይደለም ሲሉ የትግራይ ደቡባዊ ዞን የህዝብ ተወካዮች ገለጹ። የዞኑ መስተዳደር በበኩሉ አደረጃጀቱ ልማትን ለማቀላጠፍና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መሆኑን አስታውቋል፡፡ አዲሱን የወረዳ አደረጃጀት አስመልክቶ በምሁራን በተካሄደ ጥናት ላይ በዞኑ ከሚገኙ ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች የተውጣጡ የህዝብ ተወካዮች በተገኙበት በማይጨው ከተማ ትናንት ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት አዲሱ የወረዳ አደረጃጃት የህዝቡን ብዛት፣ ፍላጎት እና የቦታ ርቀት ያገናዘበ ባለመሆኑ ሊስተካከል ይገባል። በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል አቶ ወልደሰንበት ኪሮስ እንዳሉት፣ “የክልሉ መንግስት ያስጠናው አዲስ የወረዳ አደረጃጀት ህዝብን ለመጥቀም ታስቦ የተሰራ ቢሆንም የህዝቡን ቁጥርና ከመንግስታዊ መዋቅሮች ጋር ያለውን ርቀት ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” “በአዲሱ ጥናት በአንድ ወረዳ ውስጥ ከ70 እስከ 90 ሺህ ህዝብ መኖር አለበት የሚል ሀሳብ ቢቀመጥም በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው እውነታ ከተባለው ቁጥር በላይ ነው” ብለዋል። ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አያሌው ጥላሁን እንደተናገሩት፣ ቀደም ሲል በነበረው የወረዳ አወቃቃር ኦፍላወረዳ ውስጥ እንደነበሩና በአዲሱ የወረዳዎች አደረጃጀት ወደነቀሰገ ወረዳ መካተታቸውን ተናግረዋል። አደረጃጀቱ በተግባር ሲታይ በአካባቢው ያለውን መሰረተልማት እንዲሁም ርቀቱን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ነው ያመለከቱት። “በመሆኑም የክልሉ መንግስት የወረዳዎቹ አደረጃጀት የህዝቡን ፍላጎት፣ ብዛትና ርቀትን ግምት ውስጥ በማስገባትና የህዝቡን ስሜት በማዳመጥ እንደገና ሊያየው ይገባል” ብለዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሌሎች ተሳታፊዎችም አዲሱ የወረዳ አደረጃጀት የህዝቡን ስሜትና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በበኩላቸው አዲሱ የወረዳዎች አደረጃጀት የወረዳ ጥያቄን ለመመለስ ሳይሆን ልማትን ለማቀላጠፍ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተሻለ ሆኖ በመገኙ መሆኑን አስረድተዋል። የመንግስት ፍላጎት ህብረተሰቡ ብዙ ሳይጉላላ በቅርቡ ባለው የወረዳ አደረጃጀትና መዋቅር የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል። “አሁን በተደረገው የወረዳ አደረጃጃት ጥናት ርቀትም ሆነ የህዝቡን ፍላጎት ግንዛቤ ውስጥ አላስገባም የሚል ቅሬታ ካለ በቀጣይ ከህዝቡ ጋር በሚደረገው ውይይት በሚሰጥ አስተያየት መሰረት የማስተካከያ ሥራ ይሰራል” ብለዋል። አቶ ረዳኢ እንዳሉት ጥናቱ ለውይይት ክፋት ሆነ እንጂ ህዝቡ ተወያይቶ ሳያምንበት ተግባራዊ አይደረግም። በውይይት ላይ እንደተገለጸው የትግራይ ክልል በምሁራን ያስጠናው አዲስ የወረዳ አደረጃጀት ጥናት በልማትና በመልካም አስተዳደር ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል ነው። አደረጃጀቱ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ፈጣን ልማትን ለማምጣት እንዲሁም እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ህዝቡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል ያለመ መሆኑ ተገልጿል። ጥናቱ በየወረዳው ያለውን የተፈጥሮ ማዕድናት፣ የእርሻና የቱሪዝም ሀብትን ግምት ውስጥ ከማስገባቱ ባለፈ የህዝብ ብዛት፣ የመሬት ስፋት፣ ለአስተዳደር መዋቅሮች ያለውን ርቀት እና የህዝቡ ጥያቄን መሰረት ተደርጎ የተሰራ  መሆኑም በመድረኩ ላይ ተነስቷል። ህወሓት ያካሄደውን የጥልቅ ተሃድሶን ተከትሎ በክልሉ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታትና ልማትን ለማፋጠን በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በአዲስ መልክ ተቋቁመው ወደ ስራ የገቡ ተቋማት የቢሮክራሲ ውጣ ውረድን፣ የመረጃ መፋለስን በማስቀረትና ፈጣን አገልግሎትን በመስጠት ለውጥ ማምጣት መጀመራቸውን ባለፈው ሐምሌ ወር በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ ላይ መገለጹ ይታወሳል። በጉባኤው ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የወረዳዎችን አዲስ አደረጃጀት ለመተግበር በምሁራን የተካሄደ ጥናት ወደ ህዝብ ወርዶ ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድበት ጠቁመው ነበር። በትግራይ ደቡባዊ ዞን የተጀመረው ህዝባዊ ውይይትም የዚህ አካል መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም