ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደሥራ ከገባ ወዲህ የአካባቢያቸው ሰላም መሻሻሉን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደሥራ ከገባ ወዲህ የአካባቢያቸው ሰላም መሻሻሉን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
አርባ ምንጭ ነሀሴ 22 /2011---ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደሥራ ከገባ ወዲህ የአካባቢያቸው ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው መንቀሳቀስ በመጀመሩ ሰላማቸው እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በከተማው ጉርባ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ ንግስት ተፈራ ኮማንድ ፖስቱ ከመቋቋሙ በፊት በከተማው በቀን ጭምር ሲፈጸም የነበረው ንጥቂያና ዝርፊያ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ይፈጸም በነበረው የዝርፊያ ወንጀልም ብዙዎች ገንዘባቸውን፣ ጌጣጌጣቸውንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን ማጣታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ "ኮማንድ ፖስቱ ወደስራ መግባትን ተከትሎ በከተማው የነበሩ የጸጥታ ስጋቶች እየተቀረፉና የህብረተሰቡ ሰላሙ እየተሻሻለ መጥቷል" ብለዋል ፡፡ በከተማው የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ካሳሁን ደጉ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የመንግስት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለችግር ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት በመጀመሩ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ የነበረው ስጋት በአሁኑ ወቅት መቀነሱን ነው የገለጹት። ከዚህ ቀደም የፀጥታ ችግር በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉ እንዳሳዘናቸው የገለጹት ደግሞ የጫሞ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሴ ብዙነህ ናቸው፡፡ የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቀት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ወደስራ እንዲገባ ማድረጉ ተገቢ ውሳኔ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ "በቀጣይም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ " ሲሉ አረጋግጠዋል ፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳንኤል አረጋ በበኩላቸው በከተማዋ አንፃራዊ ሰላም እንዲረጋገጥ ህዝቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር በመሆን የድርሻውን በመወጣት ላይ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ የከተማዋን ሰላም ለማሻሻል በተደረገ እንቅስቃሴ ከ100 በላይ ተጠርጣሪዎች በህዝቡ ጥቆማ ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወደስ ገልጸዋል ፡፡ "የፀጥታ ሥራውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን መቆጣጠር የሚቻለው በህግ የበላይነት ብቻ ነው" ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሻምበል መስፍን አንዳርጌ ናቸው፡፡ ኮማንደር ዳንኤል እንዳሉት በከተማው ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ የፀጥታ ኃይሉን አቀናጅቶ መምራት ተችሏል። የከተማዋን ነዋሪዎች በፀጥታ ችግሮች ላይ ማወያየትና ማሳተፍ በመቻሉ የህዝቡ ሰላምና ደህንነት መረጋገጡንም አመልክተዋል፡፡ በቀጣይም ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባና የዕለት ተዕለት ሥራውን ያለስጋት በአግባቡ እንዲያከናውን ሰላሙን በማስጠበቅ በኩል ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡