በደቡብ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል---አቶ ርስቱ ይርዳው

ሀዋሳ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015-በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ከመመለስ ባለፈ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

የክልሉ መንግስት አስፈጻሚ ተቋማት የስድስት ወራት የዕቅድ ክንውን ሪፖርት ግምገማ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የህዝብን የልማት ፍላጎት ለመመለስ በተቀናጀ መንገድ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

በዚህም የአደረጃጀት ሥራዎችን ጨምሮ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በተለይም ህዝቦች ለዘመናት ሲያነሱት የነበረውን የአደረጃጀት ጥያቄ በሰከነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የዜጎችን ተጠቃሚነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ለመመለስ የተሰራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን አቶ ርስቱ ገልጸዋል።

በቀጣይ ወራቶችም እነዚህን ተግባራት በተቀናጀ መንገድ በማጠናከር ለበጀት ዓመቱ የተያዙ ዕቅዶችን ከማሳካት ባለፈ በዘላቂ ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የክልሉን መንግስት የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የፕላንና ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬ፣ በበጀት ዓመቱ በየዘርፉ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከአደረጃጀት ጀምሮ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም የልማት ሥራዎች የተከናወኑ ተግባራት ከዕቅድ አንጻር የተሻሉ እንደሆኑ በሪፖርቱ አመልክተዋል።

በተለይ በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ የታየው መነሳሳት መልካም መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ 20ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በአርሶ አደሩ ዘንድ አዳዲስ አሰራሮችን ለመልመድ እየታየ ያለው መነቃቃት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ትግል ትልቅ ስንቅ ነው ሲሉም አመልክተው "በክልሉ በሁሉም ሴክተሮች በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል" ሲሉ ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ ለግብርና መሳሪያዎች አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ዶክተር ባዩሽ፣ ከ1ሺህ በላይ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች በኪራይና ግዥ ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ከገቢ አንጻርም በግማሽ በጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርስቶች 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱ 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል ከሁሉም ሴክተር በተሰጠው ትኩረት ከ100 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አንስተው የአደረጃጀት ጥያቄን በተቀመጠውና ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ከመመለስ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች ሳይቋረጡ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ህዝቡ ከአመራሩ ጋር ከመቀናጀት ባለፈ ድጋፉን በተለያየ መንገድ እንዲያጠናክር ሃላፊዋ ጠይቀዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ የክልሉ ሁሉም አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን መድረኩም እስከ ነገ እንደሚቀጥል ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም