በህፃናት ላይ ስለሚከሰት የስኳር ህመም ግንዛቤ ማነስ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን ነው? - ኢዜአ አማርኛ
በህፃናት ላይ ስለሚከሰት የስኳር ህመም ግንዛቤ ማነስ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን ነው?
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 16 ቀን 2015 በህፃናት ላይ ስለሚከሰት የስኳር ህመም ግንዛቤ ማነስ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን ነው?
የአለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን የ2021 መረጃ እንደሚያሳየው በአለም ላይ ያሉ የስኳር ህመምተኞች ቁጥር 500 ሚሊዮን የተሻገረ ሲሆን 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች በህመሙ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከስኳር ታማሚዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚኖሩ መሆናቸውንም መረጃው ያሳያል።
የስኳር ህመም አይነት አንድ፣ አይነት ሁለትና በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት በመባል በሶስት የሚከፈል ሲሆን ከስኳር ታማሚዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት በአይነት አንድ የስኳር ህመም የተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሰባት በመቶ አካባቢ የሚሆኑት ደግሞ በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ የሚፈጠርባቸውና በአብዛኛው ጊዜያዊ የሆነና ከእርግዝና በኋላ የሚጠፋ ነው።
የአይነት አንድ የስኳር ህመም ቆሽት የተባለው የሰውነት ክፍል የሚያመርተው ኢንሱሊን የተሰኘው ንጥረ ቅመም አነስተኛ መሆን አሊያም ማምረት ሲያቆም የሚከሰት ነው።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህጻናት የሆርሞን ሃኪምና የስኳር ህሙማን ማህበር የቦርድ አባል ዶክተር ሰውአገኝ የሽዋስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የስኳር በሽታ ታካሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በተለይም አይነት አንድ የተባለው የስኳር ህመም በአብዛኛው በህጻናት ላይ እየተከሰተ መሆኑንና ማህበረሰቡ በህመሙ ላይ በቂ ግንዛቤ ያለመያዙ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ይላሉ።
በአብዛኛው ህብረተሰብ የስኳር ህመም በዘር ብቻ የሚተላለፍ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩ በርካታ ህጻናት ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ህይወታቸው ለከፋ ችግር እንዲጋለጥ እያደረገው ነውም ብለዋል።
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአይነት አንድ የስኳር ህመም በቤተሰብ ውስጥ ስኳር ህመም በሌላቸው ሰዎች እንደሚከሰትና 10 በመቶው ብቻ በዘር በመተላለፍ የሚመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአይነት አንድ የስኳር ህመም በጊዜ ከታወቀና ተገቢውን የህክምና ክትትል ከተደረገ የስኳር ህመም ከተከሰተ በኋላ ተገቢውን ህክምናና ክትትል ካልተደረገ የነርቭ ችግር አልፎ አልፎም የዕይታ እክልና የእግር በሽታ ያመጣል።
የዓለም ጤና ድርጅት የስኳር ህመም በዓለማችን ትልቁ የዕይታ ማጣት ምክንያት እንደሆነና ለልብ በሽታ፣ ለደም ግፊትና ለእግር መቆረጥ እንደሚያጋልጥ መረጃው ያትታል።
የስኳር ህመም ግንዛቤ ማነስ ህጻናትን ለውስብስብ ችግር ከመዳረጉም ባለፈ አምራች ሃይልን እንደሚጎዳ ተናግረዋል።
አብዛኛው ህጻናት ህመሙ ከታየባቸው ረጅም ጊዜ ካስቆጠረ በኋላ ወደ ህክምና ተቋም ስለሚመጡ ከህመሙ ለማገገም ጊዜ ይወስድባቸዋል።
ነገር ግን ህመሙ በጊዜ ከታወቀና ትክክለኛውን የህክምና ክትትል ከተደረገ ረጅም አመት ከህመሙ ጋር ማንኛውንም ማህበራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ መኖር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
አይነት አንድ ስኳር ህመም አጣዳፊ በመሆኑ ህፃናት ላይ የከፋ ችግር እንዳያስከትል ወላጆች የስኳር ህመም ምልክቶችን በሚያስተውሉበት ጊዜ ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዲቀንሱም መክረዋል።
በኢትዮጵያ የስኳር ህሙማን ማህበር ብቻ በአሁኑ ወቅት ከ10 ሺ በላይ ህጻናት የኢንሱሊን አቅርቦት እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ሲሆን 80 በመቶ የሚሆኑት የአይነት ሁለት የስኳር ህሙማን መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የአመጋገብ ዘይቤን ጤናማ በማድረግ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማዘውተርና ከተለያዩ ሱሶች በመራቅ ከ80 በመቶ በላይ የአይነት ሁለት የስኳር ህመምን መከላከል እንደሚቻልም ተመላክቷል።