ቻይና ያደጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲያሟሉ ጥሪ አቀረበች

751

ጥቅምት 30/2015(ኢዜአ) ቻይና ያደጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲያሟሉ ጥሪ አቀረበች።

በግብጽ ሻርም አል ሼክ እየተካሄደ በሚገኘው የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የቻይና የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ ተወካይ ዢ ዚንኋ የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቃል የገቡትን ድጋፍ እንዲያሟሉ ጠይቀዋል።

አለም በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ዘርፈ ብዙ ቀውሶችን እየተጋፈጠች ትገኛለች ያሉት ዢ በተለይም በኃይልና በምግብ አቅረቦት ረገድ ያጋጠሙንን ችግሮች በመተባበርና በአንድነት ከመፍታት ውጪ አማራጭ የለንም ሲሉ አመልክተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ሁላችንም የተለያየ ኃላፊነት አለብን ሲሉም ገልጸው የበለጸጉ ሀገራት የፓሪሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገብሩ አሳስበዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መከላከያ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውንና ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር በአስቸኳይ እንዲያሟሉም ጠይቀዋል።

ቻይና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የወጣውን አለማቀፋዊ ድንጋጌ ለመተግበር እየሰራች እንደምትገኝም አንስተው ሁሉም ሀገራት የአየር ንበረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል አለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በመጠበቅ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም