የመቱ ወረዳ አርሶ አደሮች የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ አመለከቱ - ኢዜአ አማርኛ
የመቱ ወረዳ አርሶ አደሮች የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ አመለከቱ

ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) "የቡና ጥራት ማለት የቡና ዋጋ ማለት በመሆኑ ለጥራቱ መጠበቅ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው" ሲሉ የመቱ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
ቡናን ጥራት ባለው መንገድ በመልቀምና በማድረቅ በሰዓቱ ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውንም አርሶ አደሮቹ ጠቅሰዋል።
የጉጂና ኢሉባቦር ዞኖች በበጀት ዓመቱ ወደ 700 ሺህ ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ሊያቀርቡ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢሉባቦር ዞን በዚህ ዓመት 390 ሺህ ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዞኑ በ270 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ከሚገኘው የቡና ተክል በ191 ሺህ ሔክታር ላይ የሚገኘው ምርት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ምክትል ሀላፊው አስታውቀዋል።
የቡና ምርቱ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ መሰብሰብ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የቡና ጥራት ማስጠበቂያ ውይይቶችን ጨምሮ የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ የቡና ንግድ እንዲሁም ምርቱን ያለ ጊዜው ሊረከቡ የሚጥሩ ሕገ-ወጦችን የመከላከል ስራም እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የጉጂ ዞን ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የዕቅድ ዝግጅት ባለሙያ አቶ አብዲሳ ለማ ከዞኑ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ከ315 ሺህ ኩንታል በላይ የእሸትና የደረቅ ቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል ብለዋል፡፡

ከዞኑ በተያዘው አመት ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ምርት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ176 ሺህ ኩንታል ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ በመኖሩና አዳዲስ የቡና ተክሎች ምርት ለመስጠት መድረሳቸው ለአቅርቦቱ መጨመር ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አርሶ አድሮች መካከል አርሶ አደር ተማም አልይ ባለሙያዎች በሚሰጡት ትምህርት መሰረት የቡና ምርትን ጥራት ባለው መልኩ ለመሰብሰብ እየሰሩ መሆኑን ተናገረዋል።
"ከዚህ ቀደም ከምርቱ የምናገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ነበር፤ አሁን ግን ዋጋው እየተሻሻለ ተጠቃሚነታችን እየጨመረ በመሆኑ ለጥራቱ ትኩረት ሰጥተናል'' ብለዋል።
አቶ አልይ ቂጤሳ ደግሞ በዚያው በመቱ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ "ለቡና ጥራት የምንሰጠውን ትኩረት ጨምረን እየሰራን ነው" ይላሉ።
ባለፉት ዓመታት ከግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ከተጠቃሚነት ደረጃ ዝቅተኛነት የተነሳ ለቡና ጥራት እንደማይጨነቁ አንስተው አሁኑ ላይ ግን ለውጦች አሉ ብለዋል።
በአዶላ ከተማ በቡና ንግድ የተሰማሩት አቶ ብርሀኔ አሳምነው ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ 140 ኩንታል ልዩ ጣዕም ያለው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ ከአርሶ አደሩ ለመሰብሰብ ያቀዱትን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
በወረዳው በ72 ሄክታር መሬት ላይ ለጀመሩት የቡና ልማት ስራ ለ219 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደፈጠሩ አስታውቀዋል፡፡