ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በአገዛዝ ዘመኑ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ተሰርቷል

ጥቅምት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በበላይነት በገዛበት ዘመን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር መስራቱን አንድ የሶሲየሎጂ ምሁር ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሲየሎጂ ዲፓርትመንት መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ብዙ አሻጥሮችን ሰርቶ አልፏል።

ከእነዚህ አሻጥሮቹ መካከል በ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ሲሰራ የነበረውን አሻጥር አብራርተዋል።

የአሸባሪው ህወሃት አመራሮች፣ ቤተሰቦችና እነሱን የተጠጉ ግለሰቦች በተለየ መንገድ ወደ መበልጸግ ደረጃ ሲሸጋገሩ ሌላው የበይ ተመልካች ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚ  ዘርፍ አሸባሪውን ቡድን የተጠጉት ግለሰቦች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ፕሮፌሰር ጌትነት ያስረዱት።

ይህ አካሄድ የፈጠረው ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል ዜጎችን ለከፋ ችግር በመዳረጉ ላልተጋባ ግጭት ለመዳረግ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዜጐች መካከል ሰፊ የሃብት ልዩነት መኖሩን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ጌትነት ይህም በአገሪቱ ውስጥ ድህነትን እያባበሰና፣ በዜጎች መካከል ኢፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል ልዩነት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በአገሪቱ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የፈፀመው ምዝበራ እና ማጭበርበርም ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑ ይነገራል።

በስርቆት፣ በአጭሩ በመክበርና ባልተገባ መንገድ ሃብት ማፍራት በአሸባሪው ህወሃትና አጋሮቹ በስፋት በመስተዋሉ በኢትዮጵያ በርካታ ነገሮችን ማዛባቱን ፕሮፌሰር ጌትነት ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በበላይነት በገዛበት አጋጣሚ ከስርቆትና ዘረፋ በተጨማሪ ለእርሱ የማይመቹትን ሁሉ በማሰርና በመግደልም ብዙ ግፍ መፈፀሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም