ቀጥታ፡

በሞረትና ጅሩ ወረዳ የእጅ ቦንብ ፈንድቶ የሰው ህይወት አለፈ

ደብረ ብርሃን ፤ ነሐሴ 17/ 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ የእጅ ቦንብ ፈንድቶ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በሰባት ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ  የመረጃ ትንተና ኦፊሰር ዋና ሳጅን ዓለምፀሐይ ኃይለጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  አደጋው የደረሰው ትናንት   ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ነው።

አደጋው ሊደርስ የቻለው በወረዳው ጁሁር ከተማ ከሴዓምባ ቀበሌ አንድ ግለሰብ በህገ ወጥ መንገድ የታጠቀው  የእጅ ቦንብ መጠጥ ቤት ውስጥ ድንገት በመፈንዳቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም  የእጅ ቦንቡን ይዞ የነበረው ግለሰብ ወዲያውኑ ህይወቱ ሲያልፍ፣ በዙሪያው የነበሩ አራት ግለሰቦች ከባድ እና ሦስት ግለሰቦች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች በደብረ ብርሃን እና ደነባ ሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም ዋና ሳጅን ዓለምፀሐይ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም