የኒያ ፋውንዴሽን እና የጆይ ኦውቲዝም ማዕከል መሥራች ወ/ሮ ዘሚ የኑስ በኮቪድ 19 ህመም ሳቢያ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኒያ ፋውንዴሽን እና የጆይ ኦውቲዝም ማዕከል መሥራች ወ/ሮ ዘሚ የኑስ በኮቪድ 19 ህመም ሳቢያ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) የኒያ ፋውንዴሽን እና የጆይ ኦውቲዝም ማዕከል መሥራች ወይዘሮ ዘሚ የኑስ በኮሮና ቫይረስ ፅኑ ህክምና ማዕከል ውስጥ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ።
ዛሬ ከቀኑ 6:00 ሰዓት ጀምሮ ሣር ቤት አካባቢ በሚገኘው ኒያ ፋውንዴሽን ለወይዘሮ ዘሚ የክብር አሸኛኘት እንደሚደረግም ታውቋል።
ወይዘሮ ዘሚ ወንድ ልጃቸው ያጋጠመውን የአዕምሮ ዕድገት ዝግመት መነሻ በማድረግ ህብረተሰቡ ስለ ችግሩ በጥልቀት እንዲረዳ በማስገንዘብና ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ልጆችም ድጋፍ እንዲያገኙ ፋውንዴሽን አቋቁመው እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።
ወይዘሮ ዘሚ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘው ሚሊኒየም ኮቪድ-19 ማዕከል ሲገቡ ለመላው ኢትዮጵያዊያን “በፀሎት አስቡኝ” የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ይሁንና ዛሬ ረፋድ ላይ በዚሁ የኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
በኢትዮጵያም በየቀኑ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለአገርና ለወገን ጠቃሚ ሥራ የሰሩ ዜጎችንም እያሳጣ ይገኛል።
ይሁንና በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ያለው መዘናጋት ከዚህ የበለጠ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ ነው።
ወይዘሮ ዘሚ የኑስ በአሁኑ ሰአት ከ200 በላይ ለሚሆኑ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች እንክብካቤ እያደረጉ እንደሚገኙ ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።