በመቀሌ በ117 ሚሊዮን ብር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ በ117 ሚሊዮን ብር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ተጀመረ
መቀሌ፣ ሚያዝያ 29/2013 (ኢዜአ) በመቀሌ ከተማ በ117 ሚሊዮን ብር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ስራ መጀመሩን የከተማው ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።
በመንገድ ግንባታ ስራው ከ1ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተመላክቷል።
በጊዜያዊ መስተዳድሩ የጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሃይላይ ገብረጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ስራ የተጀመረው በሰባት ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ ህዝቡ በመረጠው ቀበሌዎች ነው።
የድንጋይ ንጣፍ የመንገድ ግንባታ ስራው 15 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በመንገድ ግንባታ ስራው 1ሺህ 50 ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
“በድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታው የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ከዚህ ቀደም በ35 የልማት ቡድኖች ተደራጅተው በዘርፉ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ናቸው “ ብለዋል ።
ወጣቶቹ በመንገድ ስራ ዘርፍ ከሚያገኙት ገቢ 70 በመቶ የሚሆነውን ሌሎች ተጨማሪ የስራ ዘርፎች በመፍጠር እንዲሰማሩ ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ህይወት በላይ በሰጠችው አስተያየት “የመንገድ ስራው በቤት ውስጥ ቁጭ ብየ በመዋል ከነበረብኝ ጭንቀት አውጥቶኛል” ብላለች።
“ወደ መንገድ ስራ መግባታችን በመቀመጥ ከተፈጠረብን ጭንቀት ገላግሎናል፤ የመንገድ ስራውን በመጀመራችን ተደስተናል” ሲል በተመሳሳይ ሀሳቡን የገለጸው ደግሞ ወጣት ካህሳይ በላይ ነው።
በከተማው ባለፉት 5 ዓመታት በተከናወነ 198 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፊ መንገድ ግንባታ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸው እንደነበር በጊዜያዊ መስተዳድሩ የጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሃይላይ ገብረጊዮርጊስ አስታውቀዋል።