ሳይንስና ቴክኖሎጂ - ኢዜአ አማርኛ
ሳይንስና ቴክኖሎጂ
በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ፤ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን፥ ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Jun 11, 2026 222
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ፤ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን፥ ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን ለ5 ሚሊዮን ኮደሮች ምዕራፍ ስኬት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ውድ ኢትዮጵያውያን ለ5 ሚሊዮን ኮደሮች ምዕራፍ ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ! በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል። የ«5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች» ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ትምህርቶች 5,005,146 ሰልጣኞች ተመዝግበው ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀዋል። ይህ ስኬት የሕዝባችንን ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው አቅም ማረጋገጫ ነው። በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ፤ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን፥ ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ ነው። እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም. ድረስ የሰልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ የተሰነቀውን ግብ ለማሳካት፥ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ አካል እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ። ለወጣት ተማሪዎቻችን፤ መጭው የክረምት ወቅት ትልቅ ዕድላችሁ ነው። ጊዜያችሁን በዋዛ ከማሳለፍ ተቆጥባችሁ፤ በመመዝገብና በመማር ወደ ትምህርት ገበታችሁ ስትመለሱ ተማሪዎች ብቻ ሳትሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላችሁ የዲጂታል መሪዎች እንድትሆኑ አሳስባለሁ። ሥልጠናዎቹ ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚሰጡ ሲሆን፥ የምስክር ወረቀቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ነው። የምትገነቡት ነገ የሚጀምረው ዛሬ ነው! ለመመዝገብ እዚህ ይጫኑ: ethiocoders.et/
ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር ከፊታችን አርብ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
Jun 10, 2026 548
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፡-ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር ከመጪው አርብ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሂደውን ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በምርምርና በቴክኖሎጂ ልማት ረገድ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ይህ ዓለም አቀፋዊ የምርምር ጉባዔ እና የቴክኖሎጂ ውድድርም፤ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የጀመራቸውን የፈጠራና የምርምር ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን ይህንን ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ ተቋሙ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ዓለም አቀፋዊ የምርምር ጉባዔ እና የቴክኖሎጂ ውድድርም ከሰኔ 5 እስከ 7 2018 ዓ.ም የሚቆይ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ በጉባኤው ከ 16 አገራት የተወጣጡ ተመራማሪዎች እና ሌሎች አካላት የሚሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከላት ከ230 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገድ ችለዋል
Jun 10, 2026 428
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስራ ከጀመረበት አጭር ጊዜ ጀምሮ ከ230 ሺህ በላይ ህዝብን ማስተናገዱን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ማዕከላቱ 99 በመቶ የተገልጋዮች እርካታን ማስመገባቸውንም አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ለአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተወጠነው ይህ አዲስ መሶብ ፕሮጀክት ታላቅ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አመልክቷል። እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 11 ማዕከላትን ለመክፈት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ዘጠኙ ማለትም አራዳ፣ ቦሌ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ አዲስ ከተማ፣ ጉለሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እና የካ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት ማስገባት ተችሏል። የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ተረፈ (ኢ/ር) እንደገለጹት፣ ቀሪዎቹ የአቃቂ እና የለሚ ኩራ ማዕከላት የግንባታ አፈጻጸማቸው ከ99 ነጥብ 5 በመቶ በላይ በመሆኑ በቀጣይ ቀናት ተመርቀው አገልግሎት መጀመር የሚያስችላቸው ዝግጅት ተጠናቅቋል። ማዕከላቱ ስራ ከጀመሩበት አጭር ጊዜ ጀምሮ ከ230 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ያስተናገዱ ሲሆን፣ በተደረገው ዳሰሳም የተገልጋዮች እርካታ 99 በመቶ መድረስ መቻሉን ገልጸዋል። ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ድጋፍ የባለሙያ ቅጥር፣ ስልጠና እና መሰረታዊ ግብዓቶች ቀድመው በመሟላታቸው መሆኑንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
Jun 10, 2026 402
አዳማ ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኢትዮ - ቴሌኮም አስታወቀ። "የኢትዮ ቴሌኮም እና የፍትህ ተቋማት ጥምረት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ደህንነት" በሚል መሪ ሀሳብ በዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር እንዲሁም መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳትና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሊጋል ኦፊሰር አቶ ለማ ተሰማ፤ በቴሌኮም ዘርፍ የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ኩባንያው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለተግባራዊነቱ እየተጋ ይገኛል ብለዋል።። ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የሆኑት የቴሌኮም እና የዲጂታል አገልግሎቶች አካታች ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አንስተው በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ቀጣይ መዳረሻ እና ዲጂታል መፃዒ ዕድል የተሳካ ለማድረግ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በመቅረጽ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል። አዲሱ ስትራቴጂ “አድማስ ዲጂታል” ኢትዮ ቴሌኮምን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና በዲጂታል የጎለበተ ኩባንያ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸው ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን በማፋጠን፣ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል። በኩባንያው ያለፉት አመታት ስኬታማ ግስጋሴ ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል ያሉት አቶ ለማ፤ በተለይም የዲጂታል ፋይናንስ እና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎችን ጠቅሰዋል። በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ዘረፋና ስርቆትም ሌላኛው ችግር መሆኑን አንስተው እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል በተለይም ከፍትህ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። በኢትዮ ቴሌኮም የሕግ ጉዳዮች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ታየ፤ የስልጠና መድረኩ ያተኮረው በዲጂታል ፋይናንስ ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል እንዲሁም የቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። በሀገሪቷ የዲጂታል ፋይናንስና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል ከፍትህና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስና ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ምቹ የሚያደርጉ በርካታ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን እያከናወነ ነው
Jun 10, 2026 515
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2018 (ኢዜአ)፦የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሰራሩን ዘመናዊ ከማድረግ ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ምቹ የሚያደርጉ በርካታ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን በበይነ-መረብ ለተፈታኞች ማድረስ የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም አመልክተዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ይፋ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሀገሪቱ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ላይ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ በቅርቡ ይፋ ሆኖ በትግበራ ላይ የሚገኘው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም ሀገሪቱን በዲጂታል ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ግንባታ ዘርፍ እያከናወነችው ባለው ተግባር ዘርፈ-ብዙ ስኬቶች እየተመዘገቡበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምታደርገው በዚህ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ተቋማቸው የራሱን ሚና ለመጫወት አሰራሩን በቴክኖሎጂ የመቃኘት ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም ተቋሙ የሚሰጣቸውን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ዘመኑን የዋጁ ለማድረግ እየተቻለ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ ወቅት የተለያዩ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን በአብዛኛው በበይነ-መረብ ለተፈታኞች ማድረስ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አመልክተዋል። ከተፈታኞች ባሻገር ሌሎች አገልግሎት ፈላጊዎችም ከተቋሙ ድረ-ገጽና የበይነ-መረብ መተግበሪያዎች ጋር ተያያዥ የሆኑ ምቹ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም መሠረት ዜጎች በአካል ወደ ተቋሙ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ቦታ ሆነው፤ የጠፋባቸውን ወይም የተበላሹባቸውን የትምህርት ማስረጃዎች ማመልከትና ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር መፈጠሩን አብራርተዋል። በተጨማሪም የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ጥያቄዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል። ተቋሙ በቀጣይም ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር አብሮ ለመራመድና ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ቴክኖሎጂን የማላመድና አቅምን የማሳደግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ይህም ማህበረሰቡ ከዲጂታላይዜሽን ተጠቃሚ እንዲሆንና የተቋሙ አገልግሎት ተደራሽነት ይበልጥ እንዲሰፋ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
በክልሉ አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ ህዝብን ከወጪና እንግልት ለመታደግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
Jun 9, 2026 691
አርባ ምንጭ፤ሰኔ 2 /2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስታዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ ህዝብን ከወጪና እንግልት ለመታደግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ። በአርባ ምንጭ ከተማ የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል። ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው። በክልሉም በወላይታ ሶዶ፣ በአርባ ምንጭ እና በዲላ ከተሞች ማዕከሉን ተደራሽ በማድረግ ህዝቡ ባለበት ሆኖ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በዲጂታል ሥርአት ታግዞ የሚሰጠው አገልግሎት ለዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ጉልህ ፋይዳ አለው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ አገልግሎቱ ፈጣንና ከሙስና የጸዳ በመሆኑ የዜጎችን እርካታ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል። ማዕከሉ ዜጎች ወደክልሉ የተለያዩ ከተሞች ሳይሄዱ የፌደራል ተቋማት አገልግሎቶችን ጭምር በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል። በክልሉ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ ህዝብን ከወጪና እንግልት ለመታደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል። የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ በበኩላቸው ማዕከሉ ሰው ተኮር እንደሆነና በመንግስት አገልግሎት ላይ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን በመሠረታዊነት የሚፈታ ነው ብለዋል። የተገልጋዩን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪ የሚቀንስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ውጤታማና ለዜጎች ክብር የሰጠ አገልግሎት በመሆኑ ህዝብና መንግስትን በማቀራረብ ለሀገሪቱ ብልጽግና ጉዞ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል። "መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል" ያሉት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ ናቸው። አገልግሎቱ በዲጂታል ሥርአት የታገዘ በመሆኑ ህዝቡን በፍትሃዊነት ለማገልገል፣ መረጃን በአግባቡ ለማደራጀት እንዲሁም የተገልጋይ እንግልትን ለማስቀረት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአርባ ምንጭ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ413 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መገንባቱን ገልጸዋል። በማዕከሉ የምረቃ መርሀግብር ላይ በየደረጃው ካሉ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል። ማዕከሉ አራት የፌደራልና አምስት የክልል ተቋማትን በአንድነት ያጣመረ ሲሆን ከ32 በላይ አገልግሎቶችም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው የሚሰጡበት መሆኑ ታውቋል።
የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ የሕዝብን ሀብት ለልማት በማዋል በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Jun 8, 2026 1252
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ህዝባችን ለአገልግሎት ፍለጋ ጊዜና ገንዘቡን ሳያባክን ሃብቱን ለልማት እንዲያውል የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፤ ለህዝብ የገባነውን ቃል በተግባር መፈፀም መለያችን ነው ብለዋል። 9ኛው አዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት በየካ ክፍለ ከተማ ዛሬ መጀመሩንም አስታውቀዋል። የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ግልፅ እና ተደራሽ ለማድረግ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስራ በ2018 ዓ.ም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስራ ለማስጀመር ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ለህዝቡ ቃል በተገባው መሰረትም የዛሬውን ጨምሮ ዘጠኝ ማዕከላትን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል። ይህ አሰራር የአገልግሎት እንግልትን፣ ጉቦ የመጠየቅ ችግርን ለመቅረፍ፣ ተጠያቂነትን እና የህዝብን በክብር የመገልገል መብት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ነው ያብራሩት። ህዝቡ ለአገልግሎት ፍለጋ ጊዜውንና ገንዘቡን ሳያባክን ሃብቱን ለልማት እንዲያውል ለማድረግ የታቀደውን ግብ በማሳካት የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ከንቲባዋ ገልጸዋል። በየካ ክፍለ ከተማ ባለ 7 ወለል ህንፃ አዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ላደረጉት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማላቅ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
Jun 8, 2026 851
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማላቅ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድጉ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ። ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በየካ ክፍለ ከተማ የተገነባውን 9ኛ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል። ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት፤ የማዕከሉ መገንባት ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ግልጽ እና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩ ቀደም ሲል ከህዝብ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት የህዝብ እንግልትና ምሬት ምንጭ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን አውስተዋል። ለህዝብ ጥያቄ ቅድሚያ መስጠት ዋና መገለጫ የሆነው ከተማ አስተዳደሩ፤ ጥራት ላለው የመንግሥት አገልግሎት እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችን ነቀሶ በማውጣት እልባት እየሰጠ መምጣቱን ተናግረዋል። በዚህም አልፎ አልፎ ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የዛሬውን ጨምሮ ዘጠኝ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማደራጀት ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል። እነዚህ ማዕከላት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው እና የበቃ የሰው ሀይል የተሟሉላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። የማዕከላቱ ወደ ስራ መግባት ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበትን አሰራርን እውን በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መቅረፍ ማስቻላቸውን ነው የተናገሩት። በቀጣይም በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማላቅ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድጉ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዜጎችን ከእንግልትና ከአላስፈላጊ የገንዘብ ወጭ ታድጓል ብለዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባ የሚያደርግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ ነው
Jun 8, 2026 554
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባ የሚያደርግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ፡፡ ዶክተር ደረጄ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ በጤናው ዘርፍ ፈጣንና ቀልጣፋ የአገልግሎት ምኅዳር በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂም የጤና ተቋማትን አገልግሎት በማዘመን ወሳኝ መሰረት መጣሉን አስታውሰዋል። ለአብነትም የጤና ተቋማትን አገልግሎቶች በኦላይን የዲጂታል ሥርዓት በማሰናሰል ተገልጋዮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የኢንተርኔት አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢ የሚገኙ ጤና ተቋማት ጭምር ''በሄልዝ ኔት'' ለማስተሳሰር መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የዲጂታል ጤና አገልግሎቱም የበሽታ መከላከልና አክሞ ማዳን አቅሞችን በማጎልበት ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል። የዲጂታል ጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራትም 40 ሶፍትዌሮችን በማልማት ተገልጋዮች የጤና መረጃና አገልግሎት እንዲያገኙና መረጃን በስፋት እንዲሰንዱ እየተደረገ መሆኑን አንሰተዋል። በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባ የሚያደርግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል። በቀጣይም በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት የጤና ምኅዳሩን በዲጂታላይዜሽን የአሰራር ሥርዓት በማሳለጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ምርምሮችን ችግር ፈቺ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የትምህርት ሚኒስቴር
Jun 8, 2026 496
ሮቤ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ፣ ውጤታማና ወጥ አሠራር እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ለሀገራዊ የልማት ዕቅድ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለተመራማሪዎችና ለመምህራን በዘመናዊ የምርምር ማሻሻያ ስትራቴጂዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል። በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራ አስፈጻሚ ሰራዊት ሐንድሶ (ዶ/ር) በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ። "የሀገራት ዕድገት ዋና ምስጢር ጥራት ያለው የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ውጤት ነው" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከአካባቢያቸው ባለፈ ለሀገሪቱ የልማት ግብ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው ብለዋል። ሥልጠናውም ምሁራን በየጊዜው ከሚለዋወጡ ዓለም አቀፋዊ የምርምር ስልቶች ጋር እንዲራመዱ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ ጥራት ያለው ሥልጠና ከመስጠት ጎን ለጎን የተጀመረውን ሀገራዊ ልማት ለመደገፍ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ በትኩረት እየሠራባቸው ከሚገኙ ዋና ዋና የምርምር ዘርፎች መካከል ግብርና፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ጤና እና ቱሪዝም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ቀደም ሲል በተናጠል ይሰሩ የነበሩ የምርምር ሥራዎችን በማቀናጀት፣ የተሻለ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ግዙፍ የምርምርና የፕሮጀክት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ሥልጠናውም ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር)፤ ይህ ዓይነቱ ሥልጠና በጀትን በቁጠባ በመጠቀም ተወዳዳሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ የምርምር ውጤቶችን ለማፍራት የሰው ኃይል አቅምን እንደሚገነባ ገልጸዋል። ሥልጠናው በተለይም በመሠረታዊ የምርምር ሥርዓትና በምርምር ሥነ-ምግባር፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ በምርምር ፈንድ አፈላለግ ስልቶች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር "ኢቲቱ" የተሰኘ ወተትን ማርጋት የሚያስችል የፕሮ ባዮቲክ እርሾ ይፋ አደረገ
Jun 8, 2026 312
አዲስ አበባ፤ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር "ኢቲቱ" የተሰኘና ወተትን ለማርጋት የሚያስችል የፕሮ ባዮቲክ እርሾ ይፋ አደረገ። ኢንስቲትዩቱ አዲሱን የምርምር ውጤት ይፋ ያደረገው፣የዓለም የወተት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀ የጋራ የውይይት መድረክ እና አውደ-ርዕይ ላይ ነው። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ እንደገለጹት፤ "ኢቲቱ" የተሰኘው አዲሱ የፕሮ ባዮቲክ እርሾ በሃገሪቱ ያሉ የወተት ማቀነባበሪያ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ ከውጭ አስገብተው የሚጠቀሙበትን እርሾ የሚተካ ነው። ይህ የምርምር ውጤት የወተት ማቀነባበሪያዎችን የውጪ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ፣ፓስቸራይዝድ የተደረገ ወተትን በአራት ሰዓታት ውስጥ ማርጋት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። ኢንስቲትዩቱ ምርምር ከሚያደርግባቸው የግብርና ውጤቶች ውስጥ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸው፤ ምርቱ ለምግብ ዋስትና እና ለጤንነት ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑን አብራርተዋል። ኢንስቲትዩቱ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በወተት ምርታማነት ላይ ትኩረት ያደረጉ በባዮ ቴክኖሎጂ የታገዙ ልዩ ልዩ ምርምሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። የዓለም የወተት ቀን የወተት ምርት ለሥነ-ምግብ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ የሚታሰብበት ሲሆን፣ ዕለቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እና የግብርና ድርጅት (FAO) አማካኝነት እ.ኤ.አ በ2001 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ሁነት መሆኑ ይታወቃል።
የተገልጋይ እንግልትን ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ተግባራዊ ሆኗል
Jun 7, 2026 1120
አዳማ፤ ግንቦት 30/2018 (ኢዜአ):- በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ሕገወጥነትና የተገልጋይ እንግልት ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉን የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው አዲስ ተግባራዊ ባደረገው ‘ኦሮ ዲጂታል ቲኬት’ አገልግሎት እና ዘርፉን ለማዘመን እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል። የኤጀንሲው ኃላፊ ከማል ማሜ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምቹ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ ‘ኦሮ ዲጂታል ቲኬት አገልግሎት’ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል። ዘመናዊ አሠራሩ በዘርፉ ሲስተዋል የነበረን ብልሹ አሠራር፣ የመልካም አሥተዳደር እጦትና የተጋልጋዮችን እንግልት በመከላከል ተጨባጭ ውጤታ እያመጣ መሆኑንም አመላክተዋል። በመናኸሪያና በአካባቢው የሚስተዋሉ ሕገወጥ ተግባራትን ለማስቀረት የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበራትና የቦርድ አመራሮች ያለቸው ሚና የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት ከ17 ሺህ በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል ሲስተሙ መግባታቸውን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር ሙስባሁዲን አብዱልመጂድ ናቸው። በቴክኖሎጂ የተደገፈው አሠራር በስምሪት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ለመለየት፣ ከመናኸሪያ ውጪ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ተከታትሎ ለመቅጣት፣ ያለአግባብ የስምሪት መውጫ መስጠት ችግርን ለማስቅረት እና አገልግሎት አሰጣጡን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ለማድረግ የጎላ ጥቅም እንዳለውም አስረድተዋል። የኦሮሚያ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ማኅበራት የቦርድ ሰብሳቢ ታምራት በየነ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው የጀመረው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ሥራ የተሽከርካሪ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣምና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን የሚመራ ኢኮኖሚ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት ይሰራል
Jun 5, 2026 1319
ጎንደር፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን የሚመራ ኢኮኖሚ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ዘርፍ የተቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በአግባቡ መተግበር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታት ያቋቋመው የቢዝነስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ጀምሯል። ዩኒቨርሲቲው የማእከሉን ተልአኮና አላማ ማሳካት እንዲቻል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ፊርማም ዛሬ አከናውኗል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን የሚመራ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል። ኢኖቬሽንን ከማበረታታትና ከመደገፍ አንጻር ለፈጠራ ሃሳቦችና ስታርታፖች ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ከምርምርና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቁርኝት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎና አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባም አመልክተዋል። ከዚህ አንጻር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠን ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ በማተኮር እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ተግባራት ሞዴል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታት ያቋቋመው የቢዝነስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል የፈጠራ ሃሳቦች በልጽገው ወደ ተግባር የሚሸጋገሩበትን ምቹ የቴክኖሎጂ አውድ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው ማእከሉ የምርምር ሃሳብ ያላቸውን ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን በመቀበል ሃሳባቸውን ወደ መሬት የሚያወርዱበትን ምቹ የቴክኖሎጂ አውድ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሰቲው ማእከሉን በቴክኖሎጂ፣ በባለሙያዎችና በዘመናዊ መሳሪያዎች በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉን ጠቁመው ስራ ፈጣሪዎች ምርምርና የፈጠራ ሃሳባቸው አድጎ ወደ ገበያ እንዲወጣ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ ማእከሉ ችግር ፈቺ የምርምር ሃሳቦች ከመደርደሪያ ወርደው ወደ ኢንዱስትሪዎችና ካምፓኒዎች እንዲሸጋገሩ ብሎም የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በመግለጽ። በማእከሉ የምረቃ ስነ ስርአት ላይ የአፍሪካ ልህቀት ማእከል ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብረሃን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በሐረሪ ክልል ከ38 ሺ 300 በላይ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደዋል- የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ
Jun 5, 2026 880
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ከ38 ሺ 300 በላይ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸውን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም ገለጹ። የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም በሰጡት መግለጫ፤ የኮደርስ ሥልጠናው የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማዳበር ረገድ እንደ አገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል። እስካሁን በኢኒሼቲቩ በተከናወነው ስራ በክልል ደረጃ ስልጠናውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል 27 ሺህ 574 የሚሆኑት የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውንም ጠቁመዋል። በመርሐ ግብሩ ፕሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስ፣ አንድሮይድና ተያያዥነት ያላቸው ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሥልጠናው ወጣቶችን የክህሎት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ፣ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። ሥልጠናው ወጣቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ዕድሉን ያላገኙ ወጣቶች በቀጣይ ተመዝግበው እንዲሰለጥኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ለተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬት የጎላ ሚና አላቸው
Jun 5, 2026 900
ጎንደር፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ለተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬት የጎላ ሚና እንዳላቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ "በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በጤና፣ በኑሮና በስነ ምህዳር ላይ ዘላቂ አቅምን መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ 32ኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ እያካሄደ ነው። ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በጉባኤው እንደገለጹት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተገኘው ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ለዲጂታል 2030 ግብ ስኬት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የላቀ አበርክቶ ሊኖራቸው ይገባል። በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቱ ትውልድ የመጪው ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት ባለቤት እንዲሆን አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አስረድተዋል። የዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ለዲጂታል ኢኮኖሚው መጠናከር መሠረት መጣሉንም ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው በፈጣንና ተለዋዋጭ አለም ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂን አስፈላጊነት በመረዳት ዩኒቨርሲቲው ምርምር ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በዚህም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምርምርና የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት በዘርፉ ብቁ ተመራማሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው ይህም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በይፋ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል። የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ የዘመኑ ትውልድ የወደፊቱን አለም መቀላቀል እንዲችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ባለቤት መሆን አለበት ብለዋል። በአለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አብዮት ኢትዮጵያ ተቀላቅላ መጓዝ ትችል ዘንድ ምሁራን በጥናትና ምርምር ማገዝ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች በሚቀርቡ የምርምር ስራዎች ላይ እየተወያዩ ነው። በጉባኤው ላይ የተዘጋጀው የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽንም በዛሬው ዕለት ለእይታ ክፍት ተደርጓል።
ኢንስቲትዩቱ በአንድ ዙር 57 ሺህ ጫጩቶችን ማስፈልፈል የሚያስችል ዘመናዊ የዶሮ ምርምርና ብዜት ማዕከል እያስገነባ ነው
Jun 5, 2026 663
ጋምቤላ ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦የጋምቤላ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአንድ ዙር 57 ሺህ ጫጩቶችን ማስፈልፈል የሚያስችል የዶሮ ምርምርና ብዜት ማዕከል በማስገንባት ላይ መሆኑን አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ በጋምቤላ ከተማ ከ58 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እያካሄደ ያለውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሂደቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ጎብኝተዋል። ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ማዕከሉ የዶሮ እርባታውን ለማዘመንና ለማስፋት ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል። በተለይም እንደ ሀገር ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን ለማጠናከር እየተተገበረ ያለውን የሌማት ትሩፋት መርሃግብር ስኬታማ ለማድረግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል። በመሆኑም የግንባታውን ሂደት በማፋጠን ወደ ስራ ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ለማዕከሉ ግንባታ መፋጠን የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሯ። የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሪያል ጂንግ፤ ኢንስቲትዩቱ በምርምር የተሻሻሉ የእንስሳትና የዕጽዋት ዝርያዎችን በማውጣት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ እያስገነባ ያለው የዶሮ ምርምርና ብዜት ማዕከል የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ ያለም መሆኑንም ተናግረዋል። በምርምር ኢንስቲትዩቱ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብዮት አለማየሁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ በአንድ ዙር 57 ሺህ ጫጩቶችን የማስፈልፈል አቅም አለው። በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ከ58 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው ማዕከሉ አሁን ላይ ግንባታው ከ80 ከመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል። የማዕከሉን 2ኛ ምዕራፍ ግንባታንም ለማስጀመር የጨረታ ሂደቱ መጠናቀቁንና በቅርቡ ስራው እንደሚጀመር አቶ አብዮት ገልጸዋል።
ባንኩ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማረጋገጥ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል
Jun 4, 2026 1631
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ከማረጋገጥ አንጻር አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከቪዛ (Visa) ኩባንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን አዲስ የግብይትና የክፍያ ካርድ አገልግሎት ዛሬ ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፤ ባንኩ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም የባንኩ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሼባማይልስ (ShebaMiles) ደንበኞች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን የቅድመ ክፍያ ቪዛ ካርድ (CBE-ET Cobranded Visa Prepaid Card) ዛሬ ይፋ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ይህ አዲስ የቪዛ ካርድ የሼባማይልስ አባላት የኢ-ኮሜርስ ክፍያዎችን በቀላሉ መፈጸም የሚያስችላቸው ሲሆን፥ በሚያደርጉት ግብይትም የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ በር ይከፍታል ብለዋል። ደንበኞች በካርዱ ግብይት በሚፈጽሙበት ወቅት የሼባማይልስ ነጥቦችን የሚያከማቹ ሲሆን፥ የተሰበሰቡትን ነጥቦች ለአውሮፕላን ትኬት መግዣና ለሌሎች የሼባማይልስ ማበረታቻ ጥቅማጥቅሞች ማዋል እንደሚችሉ አብራርተዋል። የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፤ የዚህ የቪዛ ካርድ ይፋ መሆን ለአየር መንገዱ የሼባማይልስ ደንበኞች ዘመናዊና የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በክልሉ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
Jun 4, 2026 1155
ሀዋሳ ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ፡፡ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ሀዋሳን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ጎብኝተዋል፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በክልሉ የሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ሥራ ከጀመረ በኋላ ባሉት ዘጠኝ ወራት ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ተገልጋዮች በማእከሉ በተሰጣቸው አገልግሎት እርካታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። አገልግሎቱን ወደ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ ስራ የጀመረውን የሀዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለአብነት ጠቅሰዋል። በሌሎች የክልሉ ከተሞችም አገልግሎቱን በማስፋት ህዝቡ ሳይንገላታ የተቀላጠፈ አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኝ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በግንባታ ላይ ያሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት የሚበቁ ማዕከላት መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ በሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመገኘት ከተገለገሉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ወንደሰን አሸቴ፤በማዕከሉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ወደ ማዕከሉ በመጡ በ30 ደቂቃ ውስጥ የሚፈልጉትን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ በማዕከሉ የአሻራ አገልግሎት እንዳገኙ የተናገሩት አቶ ፈጠነ አድማሱ በበኩላቸው በአጭር ጊዜ የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉዳያቸውን በጊዜ ጨርሰው ወደ ሌላ የዕለት ተግባራቸው መሄድ እንደቻሉም አስረድተዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግልፅና የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት መቻሉ በራሱ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው የሲዳማና የሀዋሳ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ማዕከላትን እንዲሁም በወንዶ ገነትና ለኩ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ ማዕከላትን የተመለከቱ ሲሆን ሌሎች የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የዜጎችን እንግልት እያስቀረ ነው
Jun 4, 2026 1197
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የዜጎችን እንግልት እያስቀረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባዋ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተገነባውን መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት መርቀው ከፍተዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ የመንግሥት አገልግሎቶችን ፍትሀዊነት የሚያረጋግጥ ቀልጣፋና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ ምኅዳር እየተፈጠረ ነው። የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ህብረተሰቡ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያጋጥመውን የመልካም አስተዳደር ችግር በማስቀረት አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትንም ከአንድ ማዕከል ወደ ተንቀሳቃሽ በማሸጋገር የተደራሽነት አድማሱን የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ከተማ አስተዳደሩ የአዲስ አበባን የመንግሥት አገልግሎቶች ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የወሰደውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስረድተዋል። ለምረቃ የበቃው የኮልፌ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ለህብረተሰቡ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ የተገነባ መሆኑን አብራርተዋል። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን እንግልት እያስቀረ ያለ ውጤታማ ስራ ነው ብለዋል። በዚህም በመዲናዋ የመሶብ አንድ ማዕከላት ተደራሽነትን በማስፋትና የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የመፈፀም ውጤታማነትን እያሻሻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ወልደ ሚካኤል፤ የኮልፌ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የክፍለ ከተማውን አገልግሎቶች ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎች ሽግግርን እያጠናከረ ነው
Jun 4, 2026 424
ሐረር፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ) ፡-የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት መለዋወጥን መቋቋም በሚችሉና ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ የግብርና ምርቶች ላይ የሚያከናውነውን የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝዳንት ይስሃቅ ዩስፍ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር አብሮ የሚሄዱ የሰብል ዝርያዎችና የእንስሳት እርባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። በተለይም በየአካባቢው የሚከሰተውን ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ሁኔታ ተቋቁመው የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ አዳዲስ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ለህብረተሰቡና ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት እንዲሁም የማስፋት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት በዘንድሮው ዓመት ብቻ የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁመው ምርት መስጠት የሚችሉ 120 ነባርና አዳዲስ የግብርና ውጤቶችን ለማህበረሰቡ ማዳረስ መቻሉን ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በጤና እና ቴክኖሎጂዎች ላይም እየሰራና እውቅና እያገኘ እንደሚገኝም አክለዋል። በተለይም በቴክኖሎጂ ረገድ የአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚና ወጪ ቆጣቢ፣ ምቹ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር የማፍለቅ ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የዕጽዋት ሳይንስ መምህርና የግብርና ምርምር ትኩረት መስክ አስተባባሪ ዮናስ ሞገስ(ዶ/ር)፤ የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና በምርትና ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ እያስከተለ ይገኛል ብለዋል። በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ጎልቶ እንደሚስተዋል ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን መስራቱን ተናግረዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት ድርቅን ተቋቁመው ምርት የሚሰጡ ሁለት የለውዝ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ዝናብ አጠር አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የማሰራጨት ስራ ማከናወኑን አንስተዋል። ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ሊቋቋሙ የሚችሉ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች ላይም ምርምሮችን በማከናወን ለተጠቃሚው የማዳረስና የማስፋት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ዘርፍም አዳዲስና የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ የምርምር ስራዎችን እያወጣ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ መምህርና ተመራማሪ ኢንጅነር ሃምዛ አህመድኑር ናቸው። በተለይም በአካባቢው በሚገኙና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቁሶችን ተጠቅሞ የመኖሪያ ቤት መገንባት የሚያስችል የምርምር ስራ ማከናወኑን የገለጹት ኢንጅነር ሃምዛ፤ ይህም እንደ ሀገር ተቀባይነት ማግኘቱንና የማስፋት ስራውም እየተከናወነ መሆኑን አክለዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 43ኛው ዓመታዊ የምርምርና የማህበረሰብ ተሳትፎ ግምገማ ጉባዔውን ሰሞኑን ማካሄዱ ይታወሳል።