ስፖርት - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት
ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ተመልሷል
Feb 1, 2026 126
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ሊቨርፑል ኒውካስትል ዩናይትድን 4 ለ 1 አሸንፏል። ማምሻውን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሁጎ ኢኪቲኬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፍሎሪያን ዊትዝ እና ኢብራሂማ ኮናቴ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። ኢኪቲኬ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል። በቅርቡ አባቱን በሞት ያጣው ኢብራሂማ ኮናቴ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በእንባ ስሜቱን ገልጿል። አንቶኒ ጎርደን ለኒውካስትል ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ከአምስቱ የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሊቨርፑል በ39 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ቀያዮቹ እ.አ.አ በ2026 የመጀመሪያ የሊግ ድላቸውን አግኝተዋል። ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ 11ኛ ድሉን አስመዝግቧል። በአንጻሩ በሊጉ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኒውካስትል ዩናይትድ በ33 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ቼልሲ ዌስትሃም ዩናይትድን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አደረገ
Jan 31, 2026 139
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ቼልሲ ከመመራት ተነስቶ ዌስትሃም ዩናይትድን 3 ለ 2 አሸንፏል። አርሰናል ሊድስ ዩናይትድን በማሸነፍ የሊጉን መሪነት አጠናከረ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ ተለያየ ማምሻውን በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጃሮድ ቦውን በ7ኛው እና ክሪሴንሲዮ ሳመርቪል በ36ኛው ደቂቃ ባስቋጠሯቸው ግቦች ዌስትሃም ዩናይትድ 2 ለ 0 መምራት ችሎ ነበር። ጆአኦ ፔድሮ በ57ኛው፣ ማርክ ኩኩሬላ በ70ኛው እና ኢንዞ ፈርናንዴዝ በ92ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች ቼልሲን አሸናፊ አድርጓል። የዌስትሃም ዩናይትዱ ተከላካይ ጂን-ክሌር ቶዲቦ በ101ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በሊጉ 11ኛ ድሉን ያስመዘገበው ቼልሲ በ40 ነጥብ ደረጃውን ከአምስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። የሁለት ግብ መሪነቱን አሳልፎ የሰጠው ዌስትሃም ዩናይትድ በ20 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። በውድድር ዓመቱም 14ኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል
Jan 31, 2026 144
አዳማ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ ገለጹ። አዳማ የስምጥ ሸለቆ የቱሪስት ከተማ መሆኗን ለማስተዋወቅ ያለመ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የምሽት የታላቁ ሩጫ ውድድው ተካሄዷል። በሩጫው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ በክልሉ የተከናወኑ የከተሞች ልማት ስራዎች ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ አስችሏል ብለዋል። በተለይም በክልሉ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን ተመራጭ የቱሪስት መደረሻ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማዕከል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከተሞች ውብ፣ ጽዱ እና ምቹ እየሆኑ መምጣታቸው የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ረገድ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል። አዳማ በተሻለ መልኩ የከተማ ልማት ስራዎች ከተከናወነባቸው ከተሞች መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው ከተማዋ ወደ ዘመናዊ ከተማነት እየተሸጋገረች መሆኑንም አስረድተዋል። በዚሁ መነሻነት ለመጀመሪያ ጊዜ የከተሞችን የኮሪደር ልማት ለማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ያለመ የምሽት የሩጫ መርሃ ግብር ዛሬ መካሄዱን ተናግረዋል። የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የአዳማ ከተማን ለነዋሪቿ ምቹ ለማድረግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማእከል እንድትሆን በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በቀጣይም ከተለመደው መንገድ በመውጣትና ሌት ከቀን በመስራት የከተማዋን ዘመናዊነት እና እድገት የሚያፋጥኑ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል። በከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን ለማሳካት ፍጥነትና ጥራት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ሃይሉ ለዚህም ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት ብለዋል። የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ በበኩላቸው ቱሪዝም የከተሞችን እድገት ከማፋጠን ባለፈ አንድነት እና ህብረትን ያጠናክራል ብለዋል። ዛሬ በአዳማ ከተማ የተካሄደው የምሸት ሩጫ ከተማዋን የበለጠ በማስተዋወቅ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ፣ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ፣ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያንን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የከተማ መስተደድሩ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
አርሰናል ሊድስ ዩናይትድን በማሸነፍ የሊጉን መሪነት አጠናከረ
Jan 31, 2026 130
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አርሰናል ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። ማምሻውን በኢላንድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ማርቲን ዙቢሜንዲ፣ ቪክቶር ዮኮሬስ፣ ጋብርኤል ጄሱስ እና የሊድስ ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ካርል ዳርሎው በራሱ ላይ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው አርሰናል በ53 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል። መድፈኞቹ በሊጉ 16ኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሊድስ ዩናይትድ በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። በሌሎች መርሐ-ግብሮች ቦርንማውዝ ዎልቭስን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ፣ ብራይተን እና ኤቨርተን አንድ አቻ ተለያይተዋል።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ ተለያየ
Jan 31, 2026 101
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና እና ባህርዳር ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መስፍን ታፈሰ በ61ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ሲዳማ ቡና መሪ ሆኗል። ከእረፍት መልስ ሰቲህ ኦሴ በ71ኛው ደቂቃ የባህር ዳር ከተማን የአቻነት ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 34 ከፍ አድርጓል። ከተከታዩ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ከአራት ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፈም። ባህርዳር ከተማ በ22 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባህርዳር ከተማ ለ11ኛ ጊዜ አቻ በመውጣት በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች አቻ የወጣ ቡድን ሆኗል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ-ግብር ሸገር ከተማ መቻልን 1 ለ 0 አሸንፏል። ቡልቻ ሹራ በ59ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። ከስምንት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሸገር ከተማ በ20 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 13 ከፍ አድርጓል። በሊጉ አራተኛ ድሉን አስመዝግቧል። ከሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገደው መቻል በ29 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በውድድር ዓመቱ ያስተናገደው ሽንፈት ብዛት አምስት ደርሷል። ቀን ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል
Jan 31, 2026 98
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 አሸንፏል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ መሐመድኑር ናስር በ64ኛው እና በ71ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ በ23 ነጥብ ደረጃውን ከ13ኛ ወደ 9ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ድሉን አስመዝግቧል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ለሰባተኛ ጊዜ የተሸነፈው ሀድያ ሆሳዕና በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Jan 31, 2026 153
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በተጠባቂው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋሩ ከመርሐ-ግብሮቹ መካከል ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 23 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ33 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። በሊጉ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች መካከል አራቱን ያሸነፈው ባህርዳር ከተማ በበኩሉ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በ10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦች ተቆጥረውበታል። ባህርዳር ከተማ በ22 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ በሊጉ ለበርካታ ጊዜ አቻ የወጣ ቡድን ነው። ሲዳማ ቡና በ17ኛ ሳምንት በነገሌ አርሲ ካስተናገደው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ድል ከቀናው ከተከታዩ ሐዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ነጥብ ከፍ ያደርጋል። በሌላ በኩል ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ መቻል ከሸገር ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። መቻል በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በስምንቱ ድል ሲቀናው አራት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 23 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 13 ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ29 ነጥብ ሶስተኛ ላይ ተቀምጧል። ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በበኩሉ በሊጉ 17 ጨዋታዎችን በማድረግ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በስድስቱ ተሸንፏል። ስምንት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል። አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ17 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው መቻል በድል ጉዞው ለመቀጠል ይፋለማል። ካሸነፈ በድጋሚ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ይመለሳል። በአንጻሩ ባለፉት ስምንት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሸገር ከተማ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና በመጠኑም ቢሆን የሚርቅበትን እድል ይሰጠዋል። እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ድሬዳዋ ከተማ በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ሲይዝ ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 20 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለፉት ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። በ17ኛ ሳምንት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሽንፈት ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
የሊጉ መሪ አርሰናል ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል
Jan 31, 2026 177
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ይፋ ሆነ በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ሊድስ ዩናይትድ የሊጉን መሪ አርሰናል ምሽት 12 ሰዓት ላይ በኢላንድ ሮድ ስታዲየም ያስተናግዳል። የዮርክሻየሩ ሊድስ ዩናይትድ በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። የሰሜን ለንደኑ አርሰናል በ50 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ባለሜዳው ሊድስ በውድድር ዓመቱ 23 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ዘጠኝ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። ተጋጣሚው አርሰናል በሊጉ ካከናወናቸው 23 ጨዋታዎች መካከል በ15ቱ ድል ሲቀናው በሶስቱ ተሸንፏል። በአምስቱ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ተጋርቷል። ሊድስ ዩናይትድ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ክልል በመጠኑም ቢሆን እንዲርቅ ያደርገዋል። ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው አርሰናል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። መድፈኞቹ ካሸነፉ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ ማድረግ ያስችላቸዋል። በሌሎች መርሐ-ግብሮች ቼልሲ ከዌስትሃም ዩናይትድ ምሽት 2 ሰዓት ከ30፣ ሊቨርፑል ከኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ብራይተን ከኤቨርተን እና ዎልቭስ ከቦርንማውዝ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋሩ
Jan 30, 2026 130
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም በ41ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ወላይታ ድቻ መሪ ሆኗል። ከእረፍት መልስ አቤነዘር ሲሳይ በ69ኛው የአዳማ ከተማን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። አዳማ ከተማ በ28 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። ዛሬ በተጀመረው 18ኛ ሳምንት ቀን ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ምድረ ገነት ሽሬ እና ኢትዮጵያ መድን ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
በተጠባቂው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ
Jan 30, 2026 127
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 አሸንፏል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ተባረክ ሄፋሞ በ49ኛው እና ጌታነህ ከበደ በ93ኛው ደቂቃ ላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል። በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ሃዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ ከነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ከፍ ብሏል። ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል። በአንጻሩ በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ26 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ምድረ ገነት ሽሬ እና ኢትዮጵያ መድን ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ምድረ ገነት ሽሬ በ22 ነጥብ 10ኛ፣ ኢትዮጵያ መድን በ19 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘዋል። ምድረ ገነት ሽሬ ባለፉት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል ርቋል። ምሽት 12 ሰዓት ላይ የተጀመረው የወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ይፋ ሆነ
Jan 30, 2026 162
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ተጋጣሚዎች ዛሬ በወጣ ድልድል ተለይተዋል። በዚሁ መሰረት ቤኔፊካ ከሪያል ማድሪድ፣ ሞናኮ ከወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ፣ ካራባግ ከኒውካስትል ዩናይትድ፣ ጋላታሳራይ ከጁቬንቱስ፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከአትላንታ፣ ክለብ ብሩዥ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቦዶ ግሊምት ከኢንተር ሚላን እና ኦሎምፒያኮስ ከባየር ሌቨርኩሰን ይጫወታሉ። የጥሎ ማለፍ ማጣሪያዎቹ በየካቲት ወር የሚካሄዱ ሲሆን በደርሶ መልስ ያሸነፉ ክለቦች ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላሉ። በማጣሪያው የሚሳተፉት ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አዲሱ የውድድር ፎርማት ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ናቸው። ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል። አርሰናል፣ ባየር ሙኒክ፣ ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን በቀጥታ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀሉ ቡድኖች ናቸው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
Jan 30, 2026 170
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በስምንቱ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ በአምስቱ አቻ ወጥቷል። በጨዋታቹ ላይ 18 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል። የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሃዋሳ ከተማ በ29 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ17 ጨዋታዎች መካከል በስድስቱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 8 ጎሎችን አስተናግዷል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ26 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሃዋሳ ከተማ በ17ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ከወጣበት ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል። በሌላኛው መርሐ-ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ከኢትዮጵያ መድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ምድረ ገነት ሽሬ በሊጉ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን አሸንፏል። በስድስቱ ጨዋታዎች ሲሸነፍ በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 13 ጎሎች ገብተውበታል። ኢትዮጵያ መድን 17 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 12 ግቦችን በ17ቱ ጨዋታዎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 15 ግቦችን አስተናግዷል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ18 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ምድረ ገነት ሽሬ ከ17ኛ ሳምንት የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ኢትዮጵያ መድን ማሸነፍ ከሶስት ነጥብ ባለፈው ከወራጅ ቀጠና እንዲርቅ ያደርገዋል። ወላይታ ድቻ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። ወላይታ ድቻ በ15 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አዳማ ከተማ በ27 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ባለፉት ሰባት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ወላይታ ድቻ ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ነው። በ17ኛ ሳምንት ከመቀሌ 70 እንደርታ አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ጥር 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። ሲዳማ ቡና ሊጉን በ33 ነጥብ ይመራል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ይገኛል።
የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫሉ አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል
Jan 29, 2026 169
ጅማ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡-በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል የሚካሔደው የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫል አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ተመላከተ። በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እየተካሄደ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ውድድር እንደቀጠለ ነው። በሀገሪቱ ያሉ 49 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ልኡካን ቡድኖቻቸውን ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ልከው ደማቅ የመክፈቻ መርሃግብር ተካሄዶ ውድድሩ እንደቀጠለ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርታዊ ውድድሩ እና ፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ ፌስቲቫሉ መካሔዱ ከስፖርታዊ ውድድሩ ባሻገር አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። ውድድሩ ለመቀራረብና ወዳጅነትን ለማጠናከር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጎን ለጎን የተለያዩ አካባቢዎች ባሕል፣ ታሪክና እሴትን ለማወቅ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት። አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ሮት ቻውል ዶያክ፤ ስፖርታዊ ውድድሩ አብሮነትንና አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል። ከተለያዩ የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተማሪዎች ውድድሩን ለማካሔድ በአንድ ቦታ መገናኘታቸው እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ለመግባባትና አካባቢዎችን ለማወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑንም አመላክቷል። በዩኒቨርሲቲው መገኘታችን የጅማ ከተማን እና ታሪካዊ ቦታዎቿን ለመጎብኘት፣ የአካባቢውን ባህልና ታሪክ ለማወቅ አስችሎናል ያለው ደግሞ ከመቅደላ አንባ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ላይ የተሳተፈው ናትናኤል ደምሌ ነው። ስፖርት ፌስቲቫሉ ሀገርን በተሻለ መንገድ ለማወቅ፣ አንድነትን ለማጠናከር፣ ወዳጅነትን ለማጎልበት የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ነው ያነሳው። ውድድሩ ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ደግሞ ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የመጡትና የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ናቸው። ኹነቱ ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ እርስበርስ ይበልጥ ለመተዋወቅ እና አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን አብደታ ፈይሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን የስፖርት ውድድር እና ፈስቲቫል ለመታደም ቡድኑን እየመሩ መምጣታቸውን ገልጸው በዚህም ጥሩ ቆይታ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። መርሃ-ግብሩ ተማሪዎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን እንዲያዳብሩ እና ታሪካዊ ስፍራዎችንም እንዲጎበኙና እንዲያውቁ ለማድረግ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ጥሎ ማለፉን ተቀላቀሉ
Jan 29, 2026 215
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ዙር መርሐ-ግብር ዛሬ ማምሻውን 18 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ተደርገዋል። በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊቨርፑል ካራባግን 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። አሌክሲስ ማካሊስተር ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ፍሎሪያን ዊትዝ፣ መሐመድ ሳላህ፣ ሁጎ ኢኪቲኬ እና ፌዴሪኮ ኪዬዛ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች ሊቨርፑል በ18 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል። ቶተንሃም ሆትስፐርስ በራንዳል ኮሎ ሙዋኒ እና ዶምኒክ ሶላንኪ ግቦች ኢንትራክት ፍራንክፈርትን 2 ለ 0 አሸንፏል። ስፐርስ በ17 ነጥብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል። በሌላ መርሐ-ግብር ባርሴሎና ኮፐንሃገንን 4 ለ 1 አሸንፏል። ቡድኑ በ16 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ 16 ውስጥ ገብቷል። እንዲሁም ቼልሲ ናፖሊን 3 ለ 2 ከሜዳው ውጪ በማሸነፍ በተመሳሳይ 16 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ጥሎ ማለፍ መግባቱን አረጋግጧል። የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን አትሌቲኮ ማድሪድ 3 ለ 2 በማሸነፍ በ16 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ በቀጥታ ጥሎ ማለፍ መግባት ችሏል። በተመሳሳይ ማንችስተር ሲቲ ጋላታሳራይን 2 ለ 0 በማሸነፍ በ16 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን በመያዝ 16 ውስጥ ገብቷል። ቤኔፊካ በስታዲዮ ደ ሉዝ በተካሄደ ጨዋታ ሪያል ማድሪድን 4 ለ 2 አሸንፏል። አንድሬስ ስጄልዴሩፕ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አናቶሊ ቶርቢን በጨዋታ እና አንጄሊስ ፓቭሊዲስ በፍጹም ቅጣት ምት ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ኪሊያን ምባፔ ሁለቱን ግቦች ለሪያል ማድሪድ ከመረብ ላይ አሳርፏል። በጨዋታው ላይ ራውል አሴንሲዮ እና ሮድሪጎ ከሪያል ማድሪድ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። በጨዋታው ላይ የቤኔፊካው ግብ ጠባቂ አናቶሊ ቶርቢ በ98ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ የቀየረበት ሁኔታ በተለየ አጋጣሚ የሚነሳ ነው። ውጤቱን ተከትሎ የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት የማጣሪያ ጨዋታ ያደርጋል። ቤኔፊካ በዘጠኝ ነጥብ 24ኛ ደረጃን በመያዝ ለጥሎ ማለፍ ማጣሪያ አልፏል። የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከኒውካስል ዩናይትድ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ቪቲንሃ ለፒኤስጂ፣ ጆሴፍ ዊሎክ ለኒውካስል ዩናይትድ ግቦቹን አስቆጥረዋል። የፒኤስጂው ኡስማን ደምበሌ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል። ፒኤስጂ እና ኒውካስል ዩናይትድ በተመሳሳይ በ14 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 11ኛ እና 12ኛ ደረጃን በመያዝ ለጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ኢንተር ሚላን፣ ጁቬንቱስ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ አትላንታ፣ ባየር ሊቨርኩሰን፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ሞናኮ፣ ጋላታሳራይ፣ ካራባግ፣ ኦሎምፒያኮስ እና ቦዶ ግሊምት ሌሎችም ለጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ያለፉ ክለቦች ናቸው። አርሰናል እና ባየር ሙኒክ አስቀድመው ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው። አርሰናል በመጨረሻ ጨዋታው ካይራት አልማቲን 3 ለ 2 አሸንፏል። ቪክቶር ዮኮሬስ፣ ካይ ሃቨርትዝ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሪካርዲኒዮ በጨዋታ እና ጆርጂኒዮ በፍጹም ቅጣት ምት ለካይራት ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። አርሰናል በ24 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በአዲሱ የውድድር ፎርማት ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል። የካዛኪስታኑ ካይራት አልማቲ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን 36ኛ ደረጃን ይዞ ከውድድሩ ተሰናብቷል። ባየር ሙኒክ ፒኤስቪ አይንድሆቨንን በጀማል ሙሲያላ እና ሃሪ ኬን ግቦች 2 ለ 1 አሸንፏል። ኢስማኤል ሳይባሪ ለፒኤስቪ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። ሳይባሪ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የነበረ ተጫዋች ነው። ባየር ሙኒክ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በአራት ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ከባለፈው የውድድር ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል። ቀሪዎቹ ስምንት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ቡድኖች በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው ወደ 16ቱ ያልፋሉ። በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በማጣሪያ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ይጫወታሉ። ከ25ኛ እስከ 36ኛ የሚያጠናቅቁ ቡድኖች ከውድድሩ ተሰናብተዋል። ናፖሊ፣ ማርሴይ፣ ኢንትራክት ፍራንክፈርት፣ አያክስ፣ ፓፎስ፣ ዩኒየን ሴይንት ጂልዋ፣ ኮፐንሃገን፣ አትሌቲኮ ቢልባኦ፣ ስላቪያ ፕራግ፣ ቪያሪያል፣ ፒኤስቪ አይንድሆቨን እና ካይራት አልማቲ ከውድድሩ የተሰናበቱ ክለቦች ናቸው። ከጥሎ ማለፉ አንስቶ ያለው የውድድር ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች
Jan 28, 2026 291
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ዙር መርሐ-ግብር ዛሬ ይካሄዳል። በዕለቱ 18 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ምሽት አምስት ላይ ይደረጋሉ። በስታዲዮ ደ ሉዝ ቤኔፊካ ከሪያል ማድሪድ ይጫወታሉ። ቤኔፊካ በስድስት ነጥብ 29ኛ፣ 15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ሪያል ማድሪድ ማሸነፍ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባዋል። አቻ ማውጣትም ሊያሳልፈው የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። ሊቨርፑል ከካራባግ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይጫወታል። ከሰባት ጨዋታዎች 15 ነጥብ ያገኘው ሊቨርፑል በ15 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ካራባግ በ10 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዟል። እንደ ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑል ካሸነፈ በቀጥታ 16 ውስጥ ይገባል። አቻ ከወጣ በሂሳባዊ ስሌት የማለፍ እድል ይኖረዋል። ኢንትራክት ፍራንክፈርት ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በ14 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባዋል። አቻ መውጣት የሌሎች ቡድኖችን ውጤት እንዲጠብቅ ያደርገዋል። የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከኒውካስትል ዩናይትድ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ፒኤስጂ እና ኒውካስትል ዩናይትድ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል። የሁለቱም ቡድኖች ወደ ጥሎ ማለፉ የመቀላቀል ሂሳባዊ ስሌት ተመሳሳይ ነው። ያሸነፈ ቡድን 16 ውስጥ ይገባል። ናፖሊ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታም ትኩረት ስቧል። የጣልያኑ ክለብ ናፖሊ በስምንት ነጥብ 25ኛ ደረጃን ይዟል። ቼልሲ በ13 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ናፖሊ በቀጥታ የጥሎ ማለፍ የመግባት እድል የለውም። ማሸነፍ በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው የሚያልፉ ክለቦችን እንዲቀላቀል ያደርገዋል። ቼልሲ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ማንንም ሳይጠብቅ ወደ ጥሎ ማለፍ እንዲገባ ያደርገዋል። ባርሴሎና፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ማንችስተር ሲቲ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና አትላንታ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ9ኛ እስከ 13ኛ ደረጃን ይዘዋል። አምስቱ ክለቦች ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ከማሸነፍ ባለፈ በነጥብ የሚበልጧቸውን ክለቦች ውጤት ይጠብቃሉ። 14ኛ እና ከዛ በታች ያሉ ክለቦች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድላቸው እጅጉን የጠበበ ነው። አርሰናል እና ባየር ሙኒክ አስቀድመው ወደ ጥሎ ማለፉ መግባታቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው። አርሰናል ከካይራት አልማቲ እና ባየር ሙኒክ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን ጋር ማምሻውን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በአራት ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ከባለፈው የውድድር ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ይገባሉ። ቀሪዎቹ ስምንት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ቡድኖች በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው ወደ 16ቱ ያልፋሉ። በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በማጣሪያ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ይጫወታሉ። ከ25ኛ እስከ 36ኛ የሚያጠናቅቁ ቡድኖች ከውድድሩ ይሰናበታሉ። ኢንትራክት ፍራንክፈርት፣ ስላቪያ ፕራግ፣ ቪያሪያል እና ካይራት አልማቲ ከውድድሩ የተሰናበቱ ክለቦች ናቸው። ከጥሎ ማለፉ አንስቶ ያለው የውድድር ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ድል ተመልሷል
Jan 27, 2026 150
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ተስፋዬ ታምራት በ78ኛው ደቂቃ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል። ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 ነጥብ ደረጃውን ከ15ኛ ወደ 11ኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉ አራተኛ ድሉን አሳክቷል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ለስምንተኛ ጊዜ የተሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በ19 ነጥብ ከነበረበት 13ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ዝቅ ብሏል። ቡናማዎቹ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፉም። ዛሬ በተደረጉ ሌሎች መርሐ-ግብሮች ነገሌ አርሲ የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታዎቹን ተከትሎ 17ኛ ሳምንት ተጠናቋል። የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄድ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
በክልሉ ሲካሄድ በቆየው ስፖርታዊ ውድድር አቅም ያላቸው ታዳጊ ስፖርተኞች ተለይተዋል
Jan 27, 2026 150
ቦንጋ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሲካሄድ የቆየው ስፖርታዊ ውድድር አቅም ያላቸው ታዳጊ ስፖርተኞች የተለዩበት መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ። ለተከታታይ ስድስት ቀናት በቦንጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቋል። በመድረኩ ማጠቃለያ ለይ የተገኙት የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፣ ስፖርታዊ ውድድሩ ለክልልና ለሀገር የሚበቁ ታዳጊ ስፖርተኞች የተለዩበት እንደሆነ ገልፀዋል። ስፖርት ከውድድርነት አልፎ የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቃ ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ያነሱት አቶ ፋንታሁን፣ የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል በህዝቦች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትንና የእርስ በእርስ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል። በተለያዩ ስፖርት ዘርፎች ክልሉን ወክለው በሀገር ደረጃ ለሚሳተፉ ስፖርተኞች መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል። የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ታሪኳ ታከለ በበኩላቸው፣ ስፖርታዊ ውድድሩ የዞኑን እና የከተማውን ያነቃቃ ነበር ብለዋል። ብዙ የባህል ልውውጥ የተካሄደበት፣ አቅምና ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን የተመለከትንበት እና በቀጣይም በዘርፉ መሰራት ያለባቸው ስራዎች የተለዩበት ነበር ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በታዳጊ ወጣቶች ምዘና በእግር ኳስ ስፖርት ዋንጫ ያነሳው የሸካ ዞን የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ዋና አሰልጣኝ ገብርኤል ዜና፣ ታዳጊ ላይ የተጀመረው ስራ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ቀጣይነት ያለው ውድድር ባለመኖሩ በርካታ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች ወደ ኋላ ይቀሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ላይ የተጀመረው ስራ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል። የሚዛን ስፖርት አካዳሚ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሌ ነገሪ በበኩላቸው፤ በ2016 ዓ.ም ከክልሉ ሁሉም ዞኖች አትሌቶችን በመመልመል ወደስራ በመግባት አሁን 38 ታዳጊዎችን በ8 የስፖርት አይነቶች እያሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል። አካዳሚው ለዚሁ ውድድር ከ35 በላይ ታዳጊዎችን ማሳተፉን ጠቁመው በውድድሩም የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል። በመዝጊያው መርሃ ግብር ላይ በባህል ስፖርቶች ውድድር፣ በባህል ፌስቲቫል፣ በታዳጊዎች ምዘና እና በሌሎችም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞችና የባህል ቡድኖች የሜዳሊያ፣ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በነገሌ አርሲ ተሸነፈ
Jan 27, 2026 172
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ነገሌ አርሲ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳዊት ተፈራ በ94ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ29 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉ ስምንተኛ ድሉን አስመዝግቧል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና 33 ነጥብ ላይ ረግቷል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ17 ነጥብ ከነበረበት 17ኛ ደረጃ ወደ 16ኛ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። ሸገር ከተማ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ስምንት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ድሬዳዋ ከተማ በ20 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሐ-ግብር ይፋ ሆነ
Jan 27, 2026 152
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በ14ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ይጀመራል። የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከየካቲት 7 እስከ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የካቲት 7 ይጀመራል በዚህም የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ36 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል። መቻል በ29 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሸገር ከተማ ይጫወታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ32 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ27 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። በሌሎች የ14ኛ ሳምንት መርሐ-ግብሮች ሐዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከሲዳማ ቡና፣ ይርጋጨፌ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከባህርዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሐ-ግብር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከነገሌ አርሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Jan 27, 2026 134
አዲስ አበባ፤ ጥር 19 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል። ከመርሐ-ግብሮቹ መካከል ነገሌ አርሲ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚገነባው ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ መቻል ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በውድድር ዓመቱ 16 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሰባቱ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 17 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ነገሌ አርሲ በ26 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች ዘጠኙን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪው ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 23 ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዷል። ሲዳማ ቡና በ33 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ነገሌ አርሲ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ ባካሄዳቸው 16 ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፎ በሰባቱ ተሸንፎ አራት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።14 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ19 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን በድል ሲወጣ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ16ቱ ጨዋታዎች ላይ 19 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 20 ጎሎች ገብተውበታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ17 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ሸገር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ16 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ድሬዳዋ ከተማ በ19 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሸገር ከተማ ባለፉት ሰባት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።