ስፖርት - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት
ሻምፒዮኑ አርሰናል የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን በድል ጀምሯል
Aug 21, 2026 436
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ መርሐ ግብር አርሰናል ኮቨንተሪ ሲቲን 3 ለ 0 አሸንፏል። ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካይ ሃቫርትዝ፣ ቡካዮ ሳካ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሃቫርትዝ በ15ኛው ደቂቃ የአዲሱን የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። የኮቨንተሪው ካሌብ ይሬንቺ በ27ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። አርሰናል በጨዋታው ከፍተኛ ብልጫ ወስዷል። አዲስ አዳጊው ኮቨንተሪ ሲቲ የግብ እድሎችን መፍጠር ተስኖታል። ሻምፒዮኑ አርሰናል የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን በድል ጀምሯል። አዲስ አዳጊው ኮቨንተሪ ሲቲ በመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል። የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ የውድድር ዘመን በሻምፒዮኑ አርሰናል እና ኮቨንተሪ ሲቲ ጨዋታ ይጀመራል
Aug 21, 2026 363
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ጅማሮውን ያደርጋል። ምሽት አራት ሰዓት ላይ አርሰናል ከኮቨንተሪ ሲቲ ጋር በኤምሬትስ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል። አርሰናል የወቅቱ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ነው። ተጋጣሚው ኮቨንተሪ ሲቲ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ተመልሷል። ሁለቱ ቡድኖች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ19ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 18 ጨዋታዎች አርሰናል 10ሩን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኮቨንተሪ ሲቲ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። አርሰናል በ18ቱ ጨዋታዎች ላይ 25 ጎሎችን ሲያስቆጥር ኮቨንተሪ ሲቲ 13 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት እ.አ.አ በ2001 ነበር። በወቅቱ ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል በዴኒስ ቤርካምፕ ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል። ኮቨንተሪ ሲቲ በዛው ዓመት ከሊጉ ወርዷል። ኮቨንተሪ በፍራንክ ላምፓርድ እየተመራ በሻምፒዮንሺፑ በ95 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመልሷል። በማይክል አርቴታ የሚመራው አርሰናል የሻምፒዮንነት ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን ከአዲስ አዳጊው ክለብ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል። ኮቨንተሪ ሲቲ በመጀመሪያው የሊግ ጨዋታው ከሊጉ የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል። የ36 ዓመቱ ቶም ብራሞል የመክፈቻውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርቱ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው
Aug 20, 2026 270
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርት ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ። የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጁ ለማድረግ ሰፊ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ይታወቃል። የስታዲየሙን ለጨዋታ ዝግጁ መሆን ከውድድር ባለፈ በተለይም ለቱሪዝም ያለውን ፋይዳ በተመለከተ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በማብራሪያቸውም የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርትም ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ማንሰራራት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል። ከእግር ኳስ ውጭም በከተማዋ የውሃ ዋና፣ የአትሌቲክስ እና የብስክሌት ውድድሮችን ለማስፋት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ነው የጠቆሙት ። በከተማዋ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ያሉ ባለ ኮከብ ሆቴሎች መኖራቸው የካፍ ባለሙያዎችን መስፈርት የሚያሟላ እና ለዘርፉ ዘላቂ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የስታዲየሙ ዝግጁነት ለሀገራዊ የስፖርት እድገት እንዲሁም ለስፖርት ቤተሰቡ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ጭምር ትልቅ የምስራች መሆኑን ጠቅሰው ለቱሪዝም ዘርፉም ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል። ስታዲየሙ የጨዋታ መስፈርቱን አሟልቶና ብቁ ሆኖ መገኘቱ ብሔራዊ ቡድኑ እና ክለቦች አህጉራዊ ጨዋታዎችን በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት የመጫወት ዕድል አመቻችቷል።
ካሜሮን ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች
Aug 17, 2026 397
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ካሜሮን ማላዊን 3 ለ 0 አሸንፋለች። ማምሻውን በሞሮኮ ራባት በሚገኘው የሙላይ አል ሀሰን ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ካሜሮን ፍጹም የበላይነትን ወስዳለች። ማሪ ንጋህ በ20ኛው እና በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ስታሳርፍ፣ ናኦሚ ንጆአ ኤቶ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ሶስተኛዋን ግብ አክላለች። ማላዊ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ብታደርግም የካሜሩንን የተከላካይ ክፍል ሰብራ ግብ ማስቆጠር አልቻለችም። ካሜሮን ውጤቱን ተከትሎ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ አንስታለች። የማይበገሩት አንበሶች ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሰው ማሸነፍ አልቻሉም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የቀረበችው ማላዊ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ይህ ድል ለካሜሩን የዋንጫ ክብር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማትንም ያስገኘ ነው። አሸናፊዋ ካሜሩን ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የሁለት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ሽልማት የምታገኝ ሲሆን፣ ይህ ስኬት ቡድኑን በቀጥታ እ.አ.አ በ2027 በብራዚል ለሚካሄደው 10ኛው የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ያረጋገጠላት ሆኗል። ከካሜሩን በተጨማሪ ግማሽ ፍጻሜ የደረሱት ማላዊ፣ ሞሮኮ እና ናይጄሪያም አፍሪካን ወክለው በዚህ ታሪካዊ የዓለም ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ። ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ማላዊ የ750 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላታል። አዘጋጇን ሞሮኮን በደረጃ ጨዋታ በመለያ ምት በመርታት ሶስተኛ የወጣችው አልጄሪያ የ550 ሺህ ዶላር ሽልማት ታገኛለች። ሞሮኮ የ300 ሺህ ዶላር ሽልማት ወደ ካዝናዋ ታስገባለች። ሞኒክ ንጎክ (ካሜሩን) የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመር ጣለች። ሚካኤሊ ቢሂና (ካሜሩን) በውድድሩ ላይ ባሳየችው ብቃት ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆናለች። ቴምዋ ቻዊንጋ (ማላዊ) አምስት ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነቱን የወርቅ ጫማ ወስዳለች። ከሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሞሮኮ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ 12 ሀገራት ተሳትፈውበታል።
በሀዋሳ ከተማ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል--ከንቲባ ጥራቱ በየነ
Aug 16, 2026 473
ሀዋሳ፤ ነሀሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- በሀዋሳ ከተማ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቸ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ። “ኮሪደር ልማት ለስፖርት ቱሪዝም” በሚል መሪ ሀሳብ የታዳጊዎችና ወጣቶች የፕሮጀክት ስፖርታዊ ውድድር በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል። በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንዳሉት፣ ወጣቶችና ሕጻናት በስፖርቱ ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ የነገ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲሆኑ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በከተማዋ የሚካሄዱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ወጣቶችን፣ ሕጻናትንና አረጋውያንን ታሳቢ ያደረጉ ምቹ የመዝናኛ፣ የማረፊያና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በስፖርቱ ዘርፍ ሀዋሳ ከተማን፣ የሲዳማ ክልልንና ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት በአራት ዙር በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች 15 የሕጻናት መጫወቻ፣ የወጣቶችና ታዳጊዎች ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታዎች በዕቅድ መካተታቸውን አብራርተዋል። ከነዚህም ሦስት የታዳጊዎችና ሦስት የወጣቶች (በጠቅላላው ስድስት) ሰው ሰራሽ ሣር የተነጠፈላቸው የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ 4 የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች፣ 5 የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎችና የሜዳ ቴኒስ ማዘውተሪያዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል። እነዚህም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን አመልክተዋል። አቶ ጥራቱ አክለውም፤ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራ ከማሳለፍ በመራቅ በስፖርት ላይ እንዲያተኩሩና እነዚህን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአግባቡና በጥንቃቄ እንዲይዟቸው አሳስበዋል። የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ በላይነሽ ገዳ በበኩላቸው፣ በከተማዋ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ለአምስት ቀናት የሚቆይና በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በብስክሌትና በሜዳ ቴኒስ በሁለቱም ጾታዎች 34 ቡድኖች የሚሳተፉበት የፕሮጀክቶች ስፖርታዊ ውድድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለዘርፉ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የገለፁት ደግሞ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዶማርሶ ዶና ናቸው። በፕሮጀክት ውድድሩ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ስፖርተኞች መካከል ወጣት ፍላጎት ተሻ እና ወጣት ሚካኤል ፍጹም እንደገለጹት፣ በከተማዋ የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ባላቸው ፍላጎትና ተሰጥኦ መሠረት እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል። በክረምቱ ወቅት በተለያዩ መስኮች በፕሮጀክት ታቅፈው ሲሰለጥኑ መቆየታቸው ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ላይ እንዳያባክኑ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸውም አክለዋል። በስነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩና የክልሉ አመራሮች እንዲሁም ወጣቶች ተገኝተዋል።
አርሰናል ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 0 በማሸነፍ የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለ18ኛ ጊዜ አነሳ
Aug 16, 2026 442
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ):- አርሰናል ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ የ2026 የኤፍኤ ኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለ18ኛ ጊዜ አሳክቷል። በዌልስ መዲና ካርዲፍ በሚገኘው ታሪካዊው ፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም በተካሄደው የውድድር ዘመን መክፈቻ ጨዋታ፤አርሰናል በጨዋታው ላይ ፍጹም የበላይነት በመውሰድ ነው ማንችስተር ሲቲን ማሸነፍ የቻለው። ለአርሰናል የማሸነፊያ ግቦቹን ተከላካዩ ሪካርዶ ካላፊዮሪ፣ አጥቂው ካይ ሃቨርትዝ እና የቡድኑ አንበል ማርቲን ኦዲጋርድ አስቆጥረዋል። ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ክብር የተቀዳጀው አርሰናል እና በኤፍኤ ካፕ ፍፃሜ ቼልሲን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለዚህ ጨዋታ የበቃው ማንቸስተር ሲቲ ያደረጉት ይህ ጨዋታ፤ አርሰናል በኮሙኒቲ ሺልድ መድረክ በማንቸስተር ሲቲ ላይ ያለውን ፍጹም የበላይነት አስቀጥሏል። ሁለቱ ቡድኖች በዚሁ መድረክ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች በሙሉ አርሰናል ያሸነፈ ሲሆን፣ የዛሬው ድል በዚሁ መድረክ በማንቸስተር ሲቲ ላይ ያስመዘገበውን አራተኛ ተከታታይ ድል አድርጎታል። አርሰናል የዋንጫ ቁጥሩን ወደ 18 በማሳደግ በውድድሩ ታሪክ 21 ዋንጫዎችን በማንሳት የመጀመሪያውን ደረጃ ከያዘው ማንቸስተር ዩናይትድ ቀጥሎ ያለውን ስኬታማነት አጠናክሯል።
አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫን ለማንሳት የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Aug 16, 2026 437
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10 /2018 (ኢዜአ):- የ2026 የኮሙኒቲ ሺልድ የዋንጫ ጨዋታ በአርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ዛሬ ይካሄዳል። ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰዓት በዌልስ መዲና ካርዲፍ በሚገኘው ታሪካዊው ፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም ይካሄዳል። ይህ ተጠባቂ የውድድር ዘመን መክፈቻ ጨዋታ የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነውን አርሰናልን እና የ2026 የኤፍኤ ካፕ አሸናፊውን ማንቸስተር ሲቲን ያገናኛል። አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ክብር በመቀዳጀት፣ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በኤፍኤ ካፕ ፍፃሜ ቼልሲን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለዛሬ ጨዋታ ቀርበዋል። በኮሙኒቲ ሺልድ ታሪክ አርሰናል በማንቸስተር ሲቲ ላይ ፍጹም የበላይነት እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ። ሁለቱ ቡድኖች በዚሁ መድረክ ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በሶስቱም ጨዋታዎች አርሰናል አሸንፏል። ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2023 ባደረጉት የኮሙኒቲ ሺልድ ጨዋታ አርሰናል በመለያ ምት ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ጨዋታው ከዚህ ቀደም በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲየም ይደረግ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ዌልስ መዲና ካርዲፍ በሚገኘው ታሪካዊው ፕሪንሲፓሊቲ ስታዲየም እንዲዘዋወር ተደርጓል። ይህም የሆነበት ምክንያት በዌምብሌይ ስታዲየም ቀድሞ የተያዘ የሙዚቃ ኮንሰርት በመኖሩ እንደሆነ ታውቋል። ይህም ውድድሩ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዌልስ መዲና እንዲመለስ አድርጎታል። የ34 ዓመቱ ሳም ባሮት ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል። የኮሙኒቲ ሺልድ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1908 "የኤፍኤ ቻሪቲ ሺልድ" በሚል ስያሜ የነበረ ሲሆን በኋላም እ.ኤ.አ በ2002 አሁን ወደሚጠራበት "ኤፍኤ ኮምዩኒቲ ሺልድ" ስያሜ ተቀይሯል። ውድድሩ የሊጉን ሻምፒዮን እና የኤፍኤ ካፕ አሸናፊውን በማገናኘት አዲሱ የውድድር ዘመን በይፋ መጀመሩ የሚበሰርበት ነው። ከጨዋታው ትኬት ሽያጭ እና ማስታወቂያ የሚሰበሰበው ገቢ በሙሉ በእንግሊዝ ዙሪያ ለሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የማህበረሰብ እግር ኳስ ልማት ስራዎች ይውላል። ማንቸስተር ዩናይትድ 21 ጊዜ በማሸነፍ የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው። አርሰናል 17 ዋንጫዎችን በማንሳት ይከተላል። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ሰባት ጊዜ አሸንፏል።
የባህር ዳር ስታዲየም ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጊዜያዊ ፈቃድ አገኘ
Aug 15, 2026 254
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ስታዲየም ለ27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጊዜያዊ ፈቃድ ማግኘቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ በባህር ዳር ስታዲየም ላይ ያደረገውን ፍተሻ እና ግምገማ ተከተሎ ብሄራዊ ቡድኑ በመስከረም ወር 2019 ዓ.ም በሜዳው ለሚያደርገው ጨዋታ የሚያገለግል ጊዜያዊ የካታጎሪ 3 ፈቃድ መስጠቱን ዛሬ ለፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል። ይህ ጊዜያዊ ፈቃድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚጠብቀውን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሜዳው ጨዋታን በሀገሩ እንዲያደርግ የሚያስችለው ነው። ካፍ በስታዲየሙ የተመዘገቡ መሻሻሎችን በማድነቅ በላከው ደብዳቤ አሁንም ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጿል። የተቆጣጣሪ ቡድኑን ግኝቶችና የሚቀሩ የማስተካከያ እርምጃዎችን የያዘ ሙሉ ቴክኒካዊ ሪፖርት በቅርቡ ለፌዴሬሽኑ እንደሚላክ ገልጾ ጨዋታው በሚደረግበት ቀን የስታዲየሙን ዝግጁነት እና የደንቦች አተገባበር ለመከታተል የስታዲየም ተቆጣጣሪ ሊመድብ እንደሚችልም አስታውቋል። ካፍ አያይዞም ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለስታዲየሙ አስተዳደር እና ለሚመለከታቸው አካላት በሂደቱ ላደረጉት ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።
የ2019 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መስከረም 7 ይጀመራል
Aug 13, 2026 392
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የ2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መስከረም 7 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለአዲሱ የውድድር ዓመት ቅድመ ዝግጅታቸውን እንዲያደርጉ፤ የውድድሩን ፎርማት በተመለከተ በደርሶ መልስ ጨዋታ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክለቦችን በመጥራት ውይይት እንደሚካሄድም ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን በሶስት የአፍሪካ ዋንጫዎች የወከሉት ታዋቂው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፍስሐ ወልደአማኑኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
Aug 13, 2026 359
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ታላላቅ ተጫዋቾች አንዱ የሆኑት ፍስሐ ወልደአማኑኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። "ኳስ ፊደሉ" እና "ጠመንጃው" በሚሉ ቅጽል ስሞች የሚታወቁት አቶ ፍስሐ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታ ዘመናቸው ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥተዋል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ዋንጫዎችን አሸንፈዋል። ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይም የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ ለብሰው ተሰልፈዋል። ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ አምርተው ኑሯቸውን እዚያው ያደረጉት አቶ ፍስሐ፣ ለሀገሪቱ ክለቦች ከመጫወታቸው በተጨማሪ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን (ESFNA) መስራች አባል እና ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በህልፈታቸው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ እና ለስፖርት ቤተሰቡ መጽናናትን ተመኝቷል።
ፒኤስጂ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት ሆነ
Aug 13, 2026 398
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ መርሐ ግብር ፒኤስጂ አስቶንቪላን 2 ለ 1 አሸንፏል። ማምሻውን በኦስትሪያ በሚገኘው ሬድ ቡል አሬና በተካሄደው ጨዋታ ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ እና ዴዚሬ ዱዌ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። የ17 ዓመቱ ታዳጊ ብሪያን ማጆ የአስቶንቪላ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ጨዋታው አዝናኝ እና በርካታ የግብ እድሎች የተፈጠሩበት ነበር። ፒኤስጂ የአውሮፓ አሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫ አንስቷል። በሉሲስ ኤነሪኬ የሚመራው ፒኤስጂ ባለፈው የውድድር ዓመትም ላይ ቶተንሃምን በተመሳሳይ በመለያ ምት አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት እንደነበር የሚታወስ ነው። የፈረንሳዩ ክለብ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ዋንጫ አግኝቷል። አስቶንቪላ ዋንጫውን በብቸኝነት ያነሳው እ.ኤ.አ በ1982 ባርሴሎናን በማሸነፍ ነበር። ከ44 ዓመት በኋላ ዋንጫውን የማንሳት ህልሙ አልተሳካም። የ34 ዓመቱን ሶማሊያዊ ዳኛ ኦማር አርታን ጨዋታውን በዋና ዳኝነት መርቷል። ይህም በውድድሩ የ51 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታን የመሩ የመጀመሪያው የአውሮፓ ዜግነት የሌላቸው ዳኛ አድርጓቸዋል። የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የክለቦች ውድድር አሸናፊዎችን የሚያገናኝ የዓመቱ ማጠቃለያና አዲስ የውድድር ዘመን መክፈቻ መርሐ ግብር ነው። የጨዋታው አሸናፊው ፒኤስጂ የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኝ ሲሆን፥ ተሸናፊው አስቶንቪላ ደግሞ አራት ሚሊዮን ዩሮ ወደ ካዝናው ያስገባል።
ፒኤስጂ ከአስቶንቪላ፤ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍልሚያ
Aug 12, 2026 326
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ መርሐ ግብር ዛሬ በፒኤስጂ እና አስቶንቪላ መካከል ይደረጋል። ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ ኦስትሪያ በሚገኘው ሬድ ቡል አሬና ይካሄዳል። የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ለዚህ ጨዋታ የበቃው በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ላይ አርሰናልን በመለያ ምት አሸንፎ ዋንጫውን በማንሳቱ ነው። በሉሲስ ኤነሪኬ የሚመራው ፒኤስጂ ባለፈው የውድድር ዓመትም ላይ ቶተንሃምን በተመሳሳይ በመለያ ምት አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት እንደነበር የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል አስቶን ቪላ በአሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ መሪነት በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ የጀርመኑን ፍራይበርግ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለዛሬው ጨዋታ በቅቷል። በታሪክ አስቶን ቪላ እ.ኤ.አ በ1982 ባርሴሎናን አሸንፎ ዋንጫውን አንዴ ጊዜ አንስቷል። ፒኤስጂ እና አስቶን ቪላ ከዚህ ቀደም በአውሮፓ መድረክ የተገናኙት እ.አ.አ 2024/25 የሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ላይ ብቻ ነበር። በወቅቱ ፒኤስጂ በሜዳው 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፥ አስቶን ቪላ በቪላ ፓርክ የ3 ለ 2 ድል አስመዝግቧል። በድምር ውጤት ፒኤስጂ 5 ለ 4 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል። ይህንን ጨዋታ ይበልጥ ልዩ የሚያደርገው በዳኝነት ረገድ የሚመዘገበው አዲስ ታሪክ ነው። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) ጨዋታውን በዋና ዳኝነት እንዲመሩ የ34 ዓመቱን ሶማሊያዊ ዳኛ ኦማር አርታንን መርጧል። ይህም በውድድሩ የ51 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታን የመሩ የመጀመሪያው የአውሮፓ ዜግነት የሌላቸው ዳኛ ያደርጋቸዋል። የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የክለቦች ውድድር አሸናፊዎችን የሚያገናኝ የዓመቱ ማጠቃለያና አዲስ የውድድር ዘመን መክፈቻ መርሐ ግብር ነው። ጨዋታው መደበኛው 90 ደቂቃ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ፥ ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃ ሳይሄድ በቀጥታ ወደ መለያ ምት ያመራል። የጨዋታው አሸናፊው ቡድን የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት ሲያገኝ፥ ተሸናፊው ደግሞ አራት ሚሊዮን ዩሮ ወደ ካዝናው ያስገባል። የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ሪያል ማድሪድ ሲሆን ስድስት ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል። ባርሴሎና እና ኤሲ ሚላን በተመሳሳይ በአምስት ዋንጫዎች ይከተላሉ።
በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን አቀባበል ተደረገለት
Aug 12, 2026 330
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 6/ 2018 (ኢዜአ)፦በአሜሪካ ኦሪገን በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን አቀባበል ተደረገለት፡፡ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 1 ነሐስ በድምሩ 6 ሜዳልያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቃለች። የዘንድሮውን ውድድር አዘጋጇ አሜሪካ 24 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ በበላይነት አጠናቃለች። ኬንያ በ11 ሜዳልያ 2ኛ ሆናለች ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም 5ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች። ከሁለት ዓመት በፊት በፔሩ ሊማ በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያ 6 የወርቅ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያ በማግኘት ማጠናቀቋ ይታወሳል። ሻምፒዮናው በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት ዩጂን ከተማ ሄይዋርድ ፊልድ ከሐምሌ 29 ቀን እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ተካሂዷል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር አባል ሆነች
Aug 10, 2026 981
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (World Boxing) ባወጣው መረጃ መሰረት የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የስድስት አገራትን የአባልነት ጥያቄ ማፅደቁን አሳውቋል። ይህንኑ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ማህበሩን በመቀላቀሏ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። አክለውም፣ ይህ ለኢትዮጵያ የኩራት ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ የአፍሪካ የቦክስ ቤተሰብ ለሁላችንም የደስታና የክብር ወቅት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም በአፍሪካ ስፖርቱን የሚያጠናክር እያንዳንዱ እርምጃ ለሁሉም ድል መሆኑን ጠቅሰዋል። ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ፕሬዝዳንቱ አዲሱ ምዕራፍ ለአፍሪካ ቦክስ ታላላቅ እድሎችንና ስኬቶችን ይዞ እንደሚመጣም ያላቸውን ምኞት መግለጻቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ቻድ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ የመን እና ኩዌት ሌሎች የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር አባል የሆኑ ሀገራት ናቸው። የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (World Boxing) የተቋቋመው እ.ኤ.አ. አፕሪል 2023 ነው። ማህበሩ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቀድሞው ዓለም አቀፍ የቦክስ ማህበር (IBA) የአሰራር እና የሙስና ችግሮች ስለነበሩበት፣ ቦክስ በኦሊምፒክ ስፖርትነት የመቀጠል እድሉን ለማስጠበቅ በሚል ዓላማ ነው። ዋና መስሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ያደረገው የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (World Boxing) ዛሬ አባልነታቸው ተቀባይነት ያገኙትን ጨምሮ 168 አባል ሀገራት በስሩ ይዟል።
ለዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ39 ተጫዋቾች ጥሪ ቀረበ
Aug 10, 2026 950
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ለ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ለ39 ተጫዋቾች ዛሬ ጥሪ አድርገዋል። ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ከ20 ዓመት በታች ናሽናል ካምፕ ላይ የሚገኙ ስድስት ተጫዋቾች ይገኙበታል። ተጫዋቾቹ አርብ ነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በመሰባሰብ ዝግጅት ማድረግ እንዲጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥሪ አቅርቧል። 36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። 48 ሀገራት በ12 ምድብ ተከፍለው ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር ተደልድላለች። የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች በመስከረም ወር 2019 ዓ.ም ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ በአለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና 6 ሜዳልያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቀቀች
Aug 10, 2026 342
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው የአለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና 6 ሜዳልያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቀቃላች። ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ በተደረጉ የመጨረሻው ዕለት መርሃግብር በሁለቱም ፆታ በ1500 ሜትር ርቀት የተሳተፈችው ኢትዮጵያ ሜዳልያ ውስጥ መግባት አልቻለችም። በሴቶች ኤልሳቤት አማረ 4ኛ ፣ ሀረገወይን ካላዩ 9ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።በወንዶች ደስታው ታዴ 12ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 2 ወርቅ ፣ 3 ብር እና 1 ነሐስ አሳክታለች። ከሁለት ዓመት በፊት በፔሩ ሊማ በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያ 6 የወርቅ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያ በማግኘት ማጠናቀቋ ይታወሳል። የዘንድሮውን ውድድር አዘጋጇ አሜሪካ 24 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ በበላይነት አጠናቃለች። ኬንያ በ11 ሜዳልያ 2ኛ ሆናለች ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም 5ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች።
የክረምት ወቅት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች የወጣቶችን ስብእና የመገንባት ሚና አላቸው
Aug 9, 2026 412
ደብረ ብርሃን፤ ነሐሴ 3/2018(ኢዜአ)፡-የክረምት ወቅት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች የወጣቶችን ስብእና ለመገንባት ሚና እንዳላቸው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድርን ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ አስጀምሯል። የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማእከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው። በተለይም የስፖርት ዘርፉን በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራትና በሀገር እና ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩም ባለሀብቱንና ማህበረሰቡን በማስተባበር በየጊዜው የሚካሄዱ የታዳጊዎች ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድርን በልዩ ትኩረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል። በክረምት ወቅት ወጣቶች ገዜያቸውን የሚያሳልፉበትን ስፖርታዊ ውድድር ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተጀመረው ውድድርም የዚህ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል። የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ተክለዮሐንስ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው የክረምት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች ታዳጊዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራ እንዳያሳልፉ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። ዛሬ በተጀመረው የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ውድድር በ60 ቡድኖች የታቀፉ 1ሺህ 500 ስፖርተኞችን በማሳተፍ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል። የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች በስፖርታዊ ስነ ምግባር ከመታነጽ ባለፈ ተሰጧቸውን አውጥተው በማሳየት በቀጣይ ለትልልቅ ክለቦች የሚመረጡበትን እድል የሚከፍት ነው ብለዋል። በተለይም ስፖርት ለሰላምና ለአንድነት ያለውን አበርክቶ በመጠቀም ወጣቶች አንድነታቸውን በማጠናከር ለአካባቢያቸው ሰላምና ልማት በጋራ እንዲሰለፉ ለማድረግ እንደሚካሄድ አስረድተዋል። "የኮኮብ እግር ኳስ ቡድን" አሰልጣኝ ሐብታሙ መለሰ፣ የክረምት ውድድር መዘጋጀቱ ታዳጊዎች በስልጠና ያገኙትን የቴክኒክ እውቀት በተግባር የሚያሳዩበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል። "የአንድነት እግር ኳስ ቡድን" አሰልጣኝ ታምራት ደስታ በበኩላቸው ውድድሩ የባህል ልውውጥ በማድረግ አንድነትንና መተሳሰብን ለማጎልበት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ የተጀመረው የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ለአንድ ወር የሚካሄድ መሆኑ ተመላክቷል።
የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል
Aug 9, 2026 296
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦ 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል። ከሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በአሜሪካ ኦሬጎን እየተካሄደ ባለው ሻምፒዮና ከ147 ሀገራት የተወጣጡ ከ1800 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ኢትዮጵያም በሻምፒዮናው ላይ ተሳትፎ እያደረገች ሲሆን እስከ አሁን ሁለት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና አንድ የነሐስ በድምሩ ስድስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አሜሪካ በስምንት ወርቅ፣ ስድስት የብር እና አራት የነሐስ በድምሩ 18 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አንደኛ ደረጃን ይዛለች። ጣልያን በሶስት ወርቅ እና ሁለት ነሐስ በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እስከ አሁን 35 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል። ሻምፒዮናው ዛሬ ማምሻውን በሄይዋርድ ፊልድ ስታዲየም ይጠናቀቃል።
ኢትዮጵያ በ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ አሳካች
Aug 9, 2026 272
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦በአሜሪካ ኦሬጎን እየተካሄደ ባለው 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ አሳክታለች። ዛሬ ማለዳ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ የ3000 ሜትር ውድድር አትሌት ዮርዳኖስ ፅጋብ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች። አትሌቷ 8:43.65 የሆነ የግል ምርጥ ሰዓቷን በማስመዝገብ ነው ለሀገሯ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘቸው። ሌላኛዋ አትሌት ሽቶ ጉሚ 8:45.06 በሆነ ሰዓት ውድድሯን ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ የብር ሜዳልያ አሳክታለች። አትሌቷ በተመሳሳይ በ5000 ሜትር የብር ሜዳልያ ማግኘቷ ይታወሳል። በአሜሪካ ኦሪገን እየተከናወነ የሚገኘው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ይጠናቀቃል። ኢትዮጵያ በውድድሩ 2 ወርቅ ፣ ሦስት ብር እና 1 ነሐስ ሜዳልያ በመሰብሰብ በሜዳልያ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ብሩኖ ጉማሬሽ አርሰናልን በይፋ ተቀላቀለ
Aug 8, 2026 321
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል የኒውካስል ዩናይትድ አምበል የነበረውን የ28 ዓመቱን የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አማካይ ብሩኖ ጉማሬሽን ዝውውር ማጠናቀቁን ዛሬ ይፋ አድርጓል። የወቅቱ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው አርሰናል ለተጫዋቹ ዝውውር የ75 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ ጉማሬሽም ተጨማሪ የአንድ ዓመት ማራዘሚያ አማራጭ ያለው የአራት ዓመት ውል ተፈራርሟል። በሚኬል አርቴታ ስብስብ ውስጥ 39 ቁጥር ማሊያን ለብሶ ይጫወታል። ብሩኖ ጉማሬሽ ዝውውሩን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት አርሰናልን መቀላቀል የፈለገው አዲስ ፈተናን ለመጋፈጥ እና ትላልቅ ዋንጫዎችን ለማንሳት መሆኑን ገልጿል። የ28 ዓመቱ ተጫዋች እ.አ.አ ጁላይ 2026 ላይ አርሰናልን ለመቀላቀል በግሉ ተስማምቶ እንደነበር የሚታወስ ነው። አሁን ላይ ጉማሬሽ አርሰናልን መቀላቀሉ የተንዛዛውን የዝውውር ጉዳይ እንዲቋጭ አድርጎታል። ጉማሬሽ እ.አ.አ በ2022 ከሊዮን ወደ ኒውካስትል ዩናይትድ በመዘዋወር ሲጫወት ቆይቷል። ተጫዋቹ መድፈኞቹን መቀላቀሉ የቡድኑን የአማካይ ክፍል ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል። ብሩኖ ጉማሬሽ ከክሪስቶስ ዞሊስ እና ኢላን ሜስሊዬር በመቀጠል አርሰናል በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የተቀላቀለ ሶስተኛ ተጫዋች ሆኗል።