ስፖርት - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት
ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
Feb 8, 2026 141
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይካሄዳል። ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 11 ጊዜ ድል ሲቀናው ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 39 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 33 ጎሎችን አስተናግዷል። በ47 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ አርን ስሎት የሚመራው ሊቨርፑል በ39 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ማንችስተር ሲቲ በሊጉ እስከ አሁን ባካሄዳቸው 24 ጨዋታዎች 14 አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ በተመሳሳይ አመስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 49 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 23 ግሎች ተቆጥረውበታል። በ55 ዓመቱ ስፔናዊ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንችስተር ሲቲ በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 199 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሊቨርፑል 95 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ማንችስተር ሲቲ 51 ጊዜ ሲያሸንፍ 53 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በፕሪሚየር ሊጉ 57 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል 23 ጊዜ ሲያሸንፍ ማንችስተር ሲቲ 13 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 21 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል። በ24ኛ ሳምንት ኒውካስትል ዩናይትድን 4 ለ 1 በማሸነፍ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ሊቨርፑል የዛሬው ጨዋታ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ ለሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ነው። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወጥነት የሌለው ብቃት እያሳየ ይገኛል። በሊጉ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር ሁለት አቻ የወጣው ማንችስተር ሲቲ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የዛሬው ድል ያስፈልገዋል። ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ የሊጉ መሪ አርሰናል ጋር የሚኖረው የግብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ ይላል። የ46 ዓመቱ ክሬግ ፖውሰን ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል። በሌላኛው መርሐ-ግብር ብራይተን ከክሪስታል ፓላስ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በአሜክስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርሰናል ሰንደርላንድን በማሸነፍ የሊጉን መሪነት አጠናከረ
Feb 7, 2026 243
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አርሰናል ሰንደርላንድን 3 ለ 0 አሸንፏል። ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቪክቶር ዮኮሬስ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ማርቲን ዙቢሜንዲ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። በሊጉ 17ኛ ድሉን ያስመዘገበው አርሰናል በ56 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ ዘጠኝ ከፍ አድርጓል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሰንደርላንድ በ36 ነጥብ ከነበረበት 8ኛ ደረጃ ወደ 9ኛ ዝቅ ብሏል። በሌሎች መርሐ-ግብሮች ቼልሲ ዎልቭስን 3 ለ 1፣ ዌስትሃም ዩናይትድ በርንሌይን 2 ለ 0 እና ፉልሃም ኤቨርተንን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ቦርንማውዝ እና አስቶንቪላ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
የኢትዮጵያና የውጭ አገራት አትሌቶች የሚሳተፉበት የግማሽ ማራቶን ውድድር በሀዋሳ ይካሄዳል
Feb 7, 2026 110
ሀዋሳ ፤ጥር 30/2018 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያና የውጭ አገራት አትሌቶች የሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018” ሁለተኛው ዙር የግማሽ ማራቶን ውድድር በሀዋሳ ይካሄዳል። በነገው እለት በሀዋሳ ከተማ የሚካሄደውን “ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018” ሁለተኛው ዙር የግማሽ ማራቶን ውድድር በተመለከተ በቱሪዝም ሚኒስቴር የፕሮሞሽን ስራ አስፈጻሚ ተሾመ ተክሉ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም በነገው ውድድር የኢትዮጵያና የተለያዩ አገራት አትሌቶች እንዲሁም ከሀዋሳና የተለያዩ ከተሞች ከ500 በላይ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል። በአራት ከተሞች ብቻ ሲካሄድ የቆየው ልወቅሽ ኢትዮጵያ ውድድር ዘንድሮ ሀረርና ደብረብርሀንን በመጨመር ወደ ስድስት ከተሞች ማደጉን ገልጸው በቀጣይም በሌሎች ከተሞች የመጀመር እቅድ ተይዟል ብለዋል። ከውጪ አገራት የሚመጡ አትሌሎች በውድድሩ መሳተፋቸውም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታና የመስህብ ስፍራዎቿን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው በዚሁ መልኩ በነገው እለት ውድድሩ በሀዋሳ ከተማ ይካሄዳል ብለዋል። የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ መቅደስ ሁሪሶ፤ ሀዋሳ የፍቅር ሀይቅን ጨምሮ በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ያሏት በመሆኑ አንስተዋል። ከተማዋ በተፈጥሮ ከታደለችው መስህብ በተጨማሪ በኮሪደር ልማት ስራ ተጨማሪ ውበት እየተላበሰች ለጎብኚዎች ምቹ መሆኗን ጠቁመው ከዚህ አንፃር የውድድሩ መካሄድ ለከተማዋ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል። በሀዋሳ ከተማ ነገ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን የአዋቂዎች እንዲሁም የ8 ኪሎ ሜትር የህፃናት የሩጫ ውደድር በድምሩ ከ650 በላይ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል።
ማንችስተር ዩናይትድ አራተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ
Feb 7, 2026 117
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 2 ለ 0 አሸንፏል። በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብራያን ምቡዌሞ በ38ኛው እና ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ81ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። የቶተንሃም ሆትስፐርሱ ተከላካይ ክርስቲያን ሮሜሮ በ29ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። የተጫዋቹ መውጣት በቶተንሃም የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ዩናይትድ በ44 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። በውድድር ዓመቱ 12ኛ ድሉን አስመዝግቧል። በአንጻሩ በሊጉ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ29 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
የሊጉ መሪ አርሰናል ከሰንደርላንድ ጋር ይጫወታል
Feb 7, 2026 192
አዲስ አበባ፤ ጥር 30 /2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በዚህም መሠረት ምሽት 12 ሰዓት ላይ አርሰናል ሰንደርላንድን በኤምሬትስ ስታዲየም ያስተናግዳል። አርሰናል በ53 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ሰንደርላንድ በ36 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። መድፈኞቹ በ24ኛው ሳምንት ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ 0 በማሸነፍ ከሶስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል። አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ ዘጠነኝ ከፍ ያደርጋል። ሰንደርላንድ በ24ኛ ሳምንት በበርንሌይ ካሸነፈበት ጨዋታ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው። በሌላኛው መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ29 ነነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በጊዜያዊ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ መነቃቃትን ያሳየው ማንችስተር ዩናይትድ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታል። ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ወደ ማሸነፍ መንገድ ለመመለስ ይፋለማል። ዎልቭስ ከቼልሲ፣ ቦርንማውዝ ከአስቶንቪላ፣ ፉልሃም ከኤቨርተን እና በርንሌይ ከዌስትሃም ዩናይትድ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ኒውካስትል ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በሴይንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሊድስ ዩናይትድ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል
Feb 7, 2026 111
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ሊድስ ዩናይትድ ኖቲንግሃም ፎረስትን 3 ለ 1 አሸንፏል። በኢላንድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጄይደን ቦግል፣ ኖህ ኦካፎር እና ዶምኒክ ካልቨርት-ሉዊን የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው አጥቂው ዶምኒክ ካልቨርት-ሉዊን በዘንድሮው የውድድር ዓመት 10ኛ የሊግ ግቡን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ሎሬንዞ ሉካ ለፎረስት ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። በጨዋታው ላይ ሊድስ ዩናይትድ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል። ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሊድስ ዩናይትድ በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። በውድድር ዓመቱም ሰባተኛ ድሉን አስመዝግቧል። ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኖቲንግሃም ፎረስት በ26 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። ባለፉት ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ኖቲንግሃም ፎረስት የወራጅ ቀጠና ስጋት ውስጥ ይገኛል። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር የካቲት 1 ይጀመራል
Feb 6, 2026 112
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር ከየካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ ውድድሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። ውድድሩ "የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ ይከናወናል። ሚኒስትር ዴኤታው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድሩን ለማከናወን አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። መንግስት የስፖርት ልማት ሥራዎችን ከስፖርት መሰረተ ልማት አንስቶ በታዳጊ ልማት እና በብሄራዊ ቡድን ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በያዘው እቅድ መሠረት ታዳጊዎችን በስልጠና ማዕከላትና በአካዳሚ መልሶ በማደራጀት የስልጠና አሰጣጥ ሂደትን የማዘመንና የመፈተሽ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። ይህን መነሻ በማድረግ የዘንድሮው የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር በአዳማ ከተማ ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ታዳጊዎችን በአንድ ማዕከል ላይ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ለማድረግ ውድድሩ የላቀ ድርሻ እንዳለው ተመላክቷል። ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር የአትሌቶች የስልጠና ሂደት የሚመዘንበት፣ ተሞክሮ የሚወሰድበት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። ተተኪ ስፖርተኞች የሚመለመሉበት ውድድር ከ15 ዓመት በታች አትሌቶች የሚወዳደሩበት መሆኑ ከባለፉት ዓመታት ለየት እንደሚያደርገው በመግለጫው ወቅት ተነስቷል። በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር ሶስት ሺህ የስፖርት ልዑካን እንደሚሳተፉና በ15 የስፖርት አይነቶች ውድድሩ እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል። ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን የመጀመሪያ ዙር በድል አጠናቋል
Feb 6, 2026 115
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 አሸንፏል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የአማካይ ተጫዋቹ ኤርሚያስ ሹምበዛ በ14ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። አቡበከር አዳሙ ከኢትዮጵያ ቡና፣ መልካሙ ቦጋለ ከወላይታ ድቻ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና በ23 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 12ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል። በአንጻሩ በሊጉ ሰባተኛ ሽንፈትን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ወላይታ ድቻ ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታዎቹን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቋል። የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ዙር መርሐ-ግብር የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጀመር የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያዩ
Feb 6, 2026 88
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ታምራት እያሱ በ32ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል አርባምንጭ ከተማ መሪ ሆኗል። በ38ኛው ደቂቃ አቤል ነጋሽ የድሬዳዋ ከተማን የአቻነት ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ በ12 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዞ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ ደረጃውን ከ11ኛ ወደ 10ኛ ከፍ አድርጓል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
Feb 6, 2026 218
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ዛሬ በሊድስ ዩናይትድ እና ኖቲንግሃም ፎረስት መካከል ይካሄዳል። ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በኢላንድ ሮድ ስታዲየም ይደረጋል። ሊድስ ዩናይትድ በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ 26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 10 ጨዋታዎች ሊድስ ዩናይትድ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ኖቲንግሃም ፎረስት በአራቱ አሸንፏል። በሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ላይ ሊድስ ዩናይትድ 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት 17 ጎሎችን አስቆጥሯል። ክለቦቹ ዘንድሮ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኖቲንግሃም ፎረስት 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ሊድስ ዩናይትድ ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። በ24ኛ ሳምንት በሊጉ መሪ አርሰናል 4 ለ 0 መሸነፉ አይዘነጋም ። በ24ኛ ሳምንት ከክሪስታል ፓላስ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ኖቲንግሃም ፎረስት ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል። ሶስት ነጥብ ለሁለቱም ቡድኖች ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመራቅ ወሳኝ ነው። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ዛሬ ይጠናቀቃል
Feb 6, 2026 123
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። ከቀኑ 9 ሰዓት አርባምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች በአራቱ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በዘጠኙ ሲሸነፍ በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ11 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ18 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ድሬዳዋ ከተማ በ23 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። በ18ኛ ሳምንት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በማሸነፍ የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል። ድሬዳዋ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። በሌላ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 18 ጨዋታዎች አድርጎ አምስት ጊዜ ድል ሲቀናው በስምንቱ ተሸንፏል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 20 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡናማዎቹ በ20 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዘዋል። በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ብቻ ያሸነፈው ወላይታ ድቻ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። በ18ቱ ጨዋታዎች 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 20 ጎሎችን አስተናግዷል። ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት አራት ጨዋታዎች፣ ወላይታ ድቻ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ድል አልቀናቸውም። ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ። ጨዋታዎቹን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ይጠናቀቃል።
ነገሌ አርሲ መቀሌ 70 እንደርታን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሶስተኛ ከፍ አደረገ
Feb 5, 2026 121
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ነገሌ አርሲ መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፏል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ርሆቦት ሰላሎ በ41ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። የመቀሌ 7ዐ እንደርታው ጋትሉዋክ ቱት በ62ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ነገሌ አርሲ በ35 ነጥብ ደረጃውን ከአራተኛ ወደ ሶስተኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ 10ኛ ድሉን አሳክቷል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቀሌ 70 እንደርታ በ18 ነጥብ 17ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተገኝቷል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ዛሬ በተደረጉ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት አቻ ሲለያዩ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቅቋል። ኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ጥሏል
Feb 5, 2026 93
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ፍጹም ጥላሁን በ13ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪ ሆኗል። ይሁንና መሪነቱ የቆየው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ነው። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል በ16ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ የወልዋሎን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ፍሬው ሰለሞን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ60ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር አልቻለም። ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ17 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም። በአሁኑ ሰዓት ነገሌ አርሲ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው።
አራት ግቦች የተቆጠሩበት የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ
Feb 5, 2026 90
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት አቻ ተለያይተዋል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ግርማ ዲሳሳ እና ወንድወሰን በለጠ ለባህር ዳር ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሁዘይፋ ሻፊ እና ዩጋንዳዊው ሳይመን ፒተር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። በሊጉ ለ12ኛ ጊዜ አቻ የወጣው ባህር ዳር ከተማ በ24 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበ ቡድን ነው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎችም አቻ ወጥቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ21 ነጥብ ከነበረበት 14ተኛ ደረጃ ወደ 12ተኛ ከፍ ብሏል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።
ኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋሩ
Feb 5, 2026 103
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጓል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን በ20 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 15ኛ ከፍ አድርጓል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ ከነበረበት አራተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ከፍ ብሏል። ቡድኑ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ማስመዝገብ አልቻለም። ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በነጥብ እኩል መሆን የሚችልበትን እድልም አልተጠቀመም።
በሊጉ ነገሌ አርሲ ከመቀሌ 70 እንደርታ ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
Feb 5, 2026 111
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ምሽት 12 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ነገሌ አርሲ በሊጉ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኝ ጊዜ ሲያሸንፍ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በአምስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 20 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል። አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ32 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው መቀሌ 70 በውድድር ዓመቱ 18 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሶስቱ ድል ሲቀናው ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 13 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል። መቀሌ 70 እንደርታ በ18 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ነገሌ አርሲ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ የጣለው መቀሌ 70 እንደርታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። በሌላኛው መርሐ- ግብር ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ መድን እስከ አሁን በሊጉ 18 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ተሸንፏል። በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ18ቱ ጨዋታዎች ላይ 12 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 15 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ 16ተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል ስምንት ጊዜ ድል ሲቀናው የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎች ተቆጥረውበታል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከነማ በ32 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፋሲል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ዝቅተኛ የግብ መጠን እና ሽንፈት ያስተናገደ ቡድን ነው። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና እንዲርቅ ያደርገዋል። ፋሲል ከነማ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስት ነጥብ የመጀመሪያውን ዙር በድል ለማጠናቀቅ ያስችለዋል። በ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶችን (11) ያስመዘገበው ባህርዳር ከተማ በ23 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ባህርዳር ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል። በ18ኛ ሳምንት በነገሌ አርሲ የ2 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።
ማንችስተር ሲቲ ለካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ አለፈ
Feb 5, 2026 120
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ በካራባኦ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ኒውካስትል ዩናይትድን 3 ለ 1 አሸንፏል። ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኦማር ማርሙሽ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ቲጃኒ ራያንደርስ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል። አንቶኒ ኢላንጋ ለኒውካስትል ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። በጨዋታው ላይ ማንችስተር ሲቲ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ቢጫወትም የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ቡድኖቹ ተመጣጣኝ ነበሩ። የሲቲው አጥቂ ኦማር ማርሙሽ የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ሲቲ በአጠቃላይ ድምር ውጤት 5 ለ 1 በማሸነፍ ለካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ አልፏል። የስምንት ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ማንችስተር ሲቲ በፍጻሜው ከሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ አርሰናል ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል። የፍጻሜው ጨዋታ መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም በዌምብሌይ ስታዲየም ይካሄዳል። የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ኒውካስትል ዩናይትድ የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ተገትቷል።
ሃዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ
Feb 4, 2026 96
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሽመልስ በቀለ በ7ኛው እና ተባረክ ሄፋሞ በ14ኛው ደቂቃ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። በሊጉ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ሃዋሳ ከተማ በ35 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ከሊጉ መሪ ጋር በነጥብ እኩል ቢሆንም የግብ ክፍያ ብልጫ ተወስዶበታል። ሃዋሳ ከተማ በውድድር ዓመቱ 10ኛ ድሉን አስመዝግቧል። በአንጻሩ በሊጉ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በ28 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። በተያያዘም ዛሬ በተደረጉ የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ሀዲያ ሆሳዕና እና መቻል አንድ አቻ ሲወጡ ሸገር ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና እና መቻል አቻ ተለያዩ
Feb 4, 2026 91
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና መቻል ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቸርነት ጉግሳ በ21ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ መቻል መሪ ሆኗል። ደስታ ዋሚሾ በ32ኛው ደቂቃ ለሀዲያ ሆሳዕና የአቻነቷን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና በ21 ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 13ኛ ከፍ አድርጓል። ክለቡ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። መቻል በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። በአሁኑ ሰዓት አዳማ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ነጥብ ጣለ
Feb 4, 2026 101
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታው በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተደርጓል። ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 35 ከፍ አድርጓል። ከተከታዩ ሃዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ያገኘውን እድል አልተጠቀመም። ሲዳማ ቡና ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ27 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ላይ ድል አልቀናውም።